Wednesday, May 2, 2018

ሕወሃት ኤርትራ ጥቃት ልትፈጽምብን ትችላለች የሚል ስጋት ውስጥ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 24/2010) የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች ኤርትራ ጥቃት ልትፈጽምብን ትችላለች የሚል ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ምንጮች ገለጹ።
ጦርነቱ ቢነሳ በጦርነቱ አፍራሽ ሚና ሊኖራቸው ይችላሉ የተባሉ በርካታ መኮንኖች እየተመነጠሩ በመታሰር ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ጥቂት ወታደሮችና የበታች ሹሞችም በተመሳሳይ መታሰራቸው ታውቋል።
የሰራዊቱን መኮንኖች እየመነጠሩ የማሰሩ ርምጃ የተከተለው በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተለይም በአማራ ክልል ከወልቃይት ጋር በተያያዘ ያልተጠበቀ ተቃውሞና አመጽ ሊከተል ይችላል በሚል ስጋት ጭምር መሆኑን የመከላከያ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በዚህም የለውጥ አቀንቃኝ ተብለው የሚታመኑ እንዲሁም ለሕወሃት የጦር አዛዦች ቀና አመለካከት የላቸውም ተብለው የሚጠረጠሩትን ማሰር የተጀመረው ከወራቶች በፊት መሆኑ ታውቋል።
በአሁኑ ሰአት ደግሞ የእስር ርምጃው ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱ ተገልጿል።

እስከ ኮለኔል ማዕረግ ድረስ ባላቸው የሰራዊቱ አባላት በተለይም በኦሮሚያና አማራ ተወላጆች ላይ የተነጣጠረው የእስር ርምጃ ጥቂትም ቢሆኑ የትግራይ ተወላጆችን መጨመሩ አነጋጋሪ ሆኗል።
የታሰሩት መኮንኖችና የበታች ሹሞች እንዲሁም ተራ ወታደሮች በብዛት በወታደራዊ ሰፈሮች የታሰሩ መሆናቸው ታውቋል።
ጥቂቶቹም ወደ ክልልና ፌደራል መደበኛ እስር ቤቶች የተዛወሩ ሲሆን አመጽ በማነሳሳት በሙስናና በሌሎች ጉዳዮች ክስ እንደሚመሰረትባቸው ተመልክቷል።
በሰራዊቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ምንጠራ ትኩረት ለማስለወጥና ሰራዊቱ አቅም አለው የሚለውን ለማሳየት የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከአንዱ የጦር ክፍል ወደሌላ የጦር ክፍል በማዟዟር በሰራዊት ሰልፍ እንዲሁም በከባድ መሳሪያ አጀብ አቀባበል እያደረጉለት ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ መሪነት መድረክ ከመጡም በኋላ ሆነ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ ያላስደሰታቸው የህወሃት መሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉዞ ለመግታት ወይንም በነርሱ ፍላጎት መሰረት ለማስኬድ ያሰቡትን እቅድ እንዳያሳኩ ሶስት ጉዳዮች እንቅፋት እንደሆኑባቸውም ተመልክቷል።
ከዶክተር አብይ ጋር የሚፈጠር ውዝግብ በሃገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ በተለይም በኦሮሚያ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ዓመጽ ያቀጣጥላል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል።
በዚህ ክፍተት ኤርትራና በኤርትራ የሚደገፉ ሃይሎች ወደ ሙሉ ጦርነት ይሸጋገራሉ የሚል ስጋትና ከምዕራብ መንግስታት የሚመጣ ተቃውሞ አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተታቸውም ታውቋል።
በመሆኑም መከላከያ ሰራዊቱን ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ፍላጎትና ቁጥጥር ስር መሆኑን የማረጋገጥና በትግራይ የተቋቋመውን ልዩ ሃይል በማጠናከር ላይ መጠመዳቸው ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል በይበልጥም በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ኦሕዴድ ነጻነት እያገኘ መምጣቱና ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው በሰራዊቱ ውስጥም መነቃቃት መፍጠሩ ተመልክቷል።
በሕወሃት አመራር ውስጥ ያለውም አለመግባባት አጠቃላይ ሒደቱን ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱንም ምንጮች ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment