Wednesday, May 2, 2018

ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች እየታፈኑ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 24/2010)ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች በደህንነቶች በመታፈን ላይ መሆናቸው ታወቀ።
ከ500 በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑም የኢሳት ወኪል ያነጋገራቸው ገልጸዋል። በተለይ ከተፈናቃዮች መካከል ወንዶች እየተለዩ በመታፈን ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ከህዝብ እንዳይገናኙ በህወሃት ደህንነቶችና በኮማንድ ፖስቱ ወታደሮች ወከባ እየተደረገባቸው ነው ተብሏል።
ህወሀት የሰገሰጋቸውና በተፈናቃይ ስም የተደባለቁ የደህንነት ሰራተኞች ወደ መጣንበት እንመለስ የሚል ቅስቀሳ የጀመሩ በመሆኑ ተፈናቃዩ እንዳይታለል ጥሪ ተደርጓል።
ተፈናቃዮቹ የሚላስ የሚቀመስ በማጣታቸው ወደ ልመና መሰማራታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ባህር ዳር የገቡትና በቀናት ልዩነት የደረሱት ከ500 በላይ የአማራ ተወላጆች የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸውን ነው የኢሳት ወኪል በስፍራው ተገኝቶ ካነጋገራቸው ተፈናቃዮች መረዳት የቻለው።
እንደወኪላችን ዘገባ ከሆነ በቤንሻንጉል ጉምዝ የወረዳ አመራሮች ከጀርባ እንዳሉበትና የክልሉ ፖሊስ ድጋፍ ሰጥቶበታል በተባለው መፈናቀል ቀዬ መንደራቸውን ትተው ወደ ባህርዳር የሸሹት የአማራ ክልል ተወላጆች የወገን እጅ እየጠበቁ ነው።

ተፈናቅለው ከመጡበት ዕለት ጀምሮ ሰው እንዳያገኛቸው የተደረጉ ሲሆን ምግብና ውሃ አጥተው በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር ከ20 በላይ ሰዎች ለተገደሉበትና ለንብረት ውድመት የዳረገው ጥቃት ከተፈጸመ ወዲህ በካማሻ ዞን የአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ በደል እንደሚፈጸም የገለጹት ተፈናቃዮቹ፡ አካባቢውን ለቃችሁ ሂዱ የሚል ጫና ከአካባቢው አመራሮች ጭምር እንደሚፈጠርባቸው ገልጸዋል።
ከዚያን ወዲህ በስጋት ይኖሩ እንደነበረ የሚገልጹት ተፈናቃዮቹ ከ10 በላይ የአማራ ተወላጆች መገደላቸውንም ጠቅሰዋል።
ህይወታችን አደጋ ላይ በመውደቁ ወደ ባህርዳር ተሰደናል በማለትም የገጠማቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለወኪላችን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹ ባህርዳር ከደረሱ በኋላ ምንም አይነት መፍትሄ ከአማራ ክልል አስተዳደር እንዳላገኙም ታውቋል።
ወደ መጣችሁበት አለበለዚያም በአማራ ክልል ዘመዶቻችሁ ጋር ሂዱ የተባሉት ተፈናቃዩች ፤በኮማንድ ፖስቱ የእስር ዛቻና ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው ይገኛል።
ለኢሳት ዛሬ በደረሰው መረጃ ደግሞ በኮማንድ ፖስቱ እየተዋከቡ ያሉት ተፈናቃዮች ህወሀት ባሰማራቸው ደህንነቶች እየታፈኑ ደብዛቸው እየጠፋ ነው።
በተለይም ወንዶች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው እየተወሰዱ ሲሆን ወዴት እንደገቡ እንደማያውቁ ቤተሰቦቻቸው ለወኪላችን ገልጸዋል።
ወደ መጣችሁበት ተመለሱ የሚለውን የአማራ ክልል መንግስት ግፊት አንቀበለውም፡ እዚሁ እንደምታደርጉን አድርጉን ሲሉ ተማጽኖአቸውን አቅርበዋል።
በውስጣቸው በተፈናቃይ ስም የተሰገሰጉ የህወሃት ደህንነት ሰራተኞች ወደ መጣንበት እንመለስ የሚል ቅሰቀሳ እያደረጉ ነው ብለዋል ተፈናቃዮቹ።
በአሁን ጊዜ በባህርዳር ቅዱስ ጊዩርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ፡ በከቀበሌ 11 አባይ ማዶ ገብርኤል ቤተክርስቲያንና በባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጂ አከባቢ ሰፍረው የሚገኙት ተፈናቃዮች ምግብና ውሃ በማጣታቸው ወደ ልመና መግባታቸውን ወኪላችን ገልጿል።
በተወሰነ ደረጃ የባህርዳር ነዋሪ ድጋፍ እያደረገላቸው ቢሆንም በኮማንድ ፖስቱ ወከባ ምክንያት የሚደረግላቸውን እገዛ በአግባቡ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
ተፈናቃዮቹ ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ አናውቅም ስጋት ገብቶናል ሲሉም ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment