Thursday, May 31, 2018

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በጽሕፈት ቤታቸው ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በመወያዬታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

Image may contain: 2 people, people smiling, people standingአቶ አንዳርጋቸው ነገ ጧት ለንደን ይገባሉ። (ኢሳት ዜና ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ/ም) የግንቦት 7 ዋና ጸሀፊና የሞት ፍርድ ተላልፎባቸው ባለፉት አራት አመታት በእስር የቆዩት አቶ አንዳርጋቸው ትናንት ከቀትር በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለሁለት ሰዓታት የዘለቀ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ “መሰረታዊ ባሏቸው” ጉዳዮች ዙሪያ ስለደረጓቸው ውይይቶች ለጊዜው ለመገናኛ ብዙሀን መግለጽ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ ማህበራዊ ሚዲያው ዶክተር አብይና አቶ አንዳርጋቸው በፈገግታ ተሞልተውና እጅ ለእጅ ተጨባብጠው በሚታዩበት ፎቶ የተጥለቀለቀ ሲሆን፣ ክስተቱን እንደ ትልቅ የለውጥ ጅምር ምዕራፍ የወሰዱት ጥቂቶች አይደሉም። በኢትዮጵያውያኑ ከስተሰጡት አስተያየቶች መካከል፦ “የጥልና የጠላትነት መጋረጃ ተቀደደ፣ ይህን ፈጽሞ ማመን አንችልም! አምላክ የሀገራችንን ጸሎት ሰማት ማለት ነው? ሳቃችንን ያስመሽልን!ለውጡን የምር ያርግልን!”የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው። ላለፉት 27 ዓመታት ሥር ከሰደደው የጠላትና የመገዳደል ፖለቲካ አኳያ የትናንት ምሽቱን ክስተት ተአምር
እንደሆነባቸው የገለጹ ኢትዮጵያውያን፣ በእርግጥም ከነ ድርጅታቸው በሽብርተኝነት የተከሰሱትና የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ከመፈታታቸውም ባሻገር በቤተመንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መምከራቸው ፣ መቼም ይሆናል ተብሎ ያልተጠበቀ ተአምር ነው ብለዋል። ከትናንት ምሽት ጀምሮ የኢሳት ዝግጅት ክፍል የስልክ መልዕክት ሳጥኖችም በተመሣሳይ መል ዕክቶች ተጨናንቀዋል። አስተያዬት ሰጭዎቹ በመጨረሻም፣የዶክተር አብይ አህመድ አመራር ከሁሉም ኃይሎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥና መሰረታዊ በተባሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የለውጡን ጅምር ከዳር እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፌስቡክ ገጽ የዶክተር አብይን እና የአቶ አንዳርጋቸውን ምስክ ከቨር ፎቶ አድርጎ ሲጠቀም፣ ብአዴን በበኩሉ የዕለቱ ምርጥ ፎቶ የሚል ርዕስ ሰጥቶ በገጹ ላይ ለጥፎታል። ይህ በእንዲህ አንዳለ የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ሰሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ ማምሻቸውን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ነገ ጧት ለንደን እንደሚገቡ ታውቋል። በለንደንና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አቶ አንዳርጋቸውን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን፣ በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ያሉ ደግሞ ጊዜው ስላጠረባቸው ከቀናት በኋላ ሌላ የአቀባበል ዝግጅት እንዲደረግ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

No comments:

Post a Comment