Friday, May 25, 2018

ወይዘሮ አዜብ መስፍን የሜቴክ የቦርድ አባል ሆነው ተሾሙ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 17 /2010) የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን የሜቴክ የቦርድ አባል ሆነው ተሾሙ።
በቅርቡ የኢንደስትሪ ሚኒስተር ሆነው የተሾሙት ዶክተር አምባቸው መኮንን አቶ ደመቀ መኮንንን ተክተው የቦርድ ሊቀመንበር ሆነዋል። 
የሕወሃቱ አቶ አስመላሸ ወልደ ስላሴም የሜቴክ ቦርድ አባል ሆነዋል። ከፖለቲካ መድረኩ የተገለሉ ሰዎች ተመልሰው ወደ ሃላፊነት መምጣታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
በመንግስት 10 ቢሊዮን ብር በጀት የተቋቋመው የመሰረታዊ ብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ከፍተኛ የሃገር ሃብት ምዝበራ የሚካሄደበት ተቋም መሆኑ ሲጠቀስ ቆይቷል።
የዚህ ተቋም ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጄነራል ክንፈ ዳኘው የሕወሃት ታጋይ የነበሩ ናቸው።

በቅርቡ በፈቃዳቸው ነው በሚል ስልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን ፣በምትካቸው የኢንደስትሪ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር በቀለ ቡላዶ ተሹመዋል።
ሜቴክ ከሃገሪቱ የስኳር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በቢሊየን የሚቆጠር ሃብት በመመዝበር የሚጠቀስ ሲሆን፣በፓርላማው ጭምር ጥያቄ እንደተነሳበት ይታወቃል።
ሜቴክ የመንግስት ተቋም እንደሆነ ቢጠቀስም፣ድርጅቱን የሚመሩት ሃላፊዎች ፣ለሜቴክ የሚሰጡ ኮንትራቶችን ወደ ሕወሃት ኤፈርት እያሻገሩ የሕወሃት ኩባንያዎችን ሲያፋፉ መቆየታቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲስ ሃላፊ ለሜቲክ መሾማቸውን ተከትሎ ዘረፋው እንደሚቆም እና ከሕወሃቱ ኤፈርት ጋር ያለው ግኑኝነት እንደሚቋረጥ በብዙዎች ዘንድ ታምኖ ነበር።
አሁን ወይዘሮ አዜብ እና አቶ አስመላሸ ወልደስላሴ በሜቴክ የቦርድ አባልነት መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
የውስጥ ትግሉ ላለመቋጨቱ ማሳያ እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል። ከሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የተባረሩት የወይዘሮ አዜብ መስፍን መሾም ደግሞ ያልተጠበቀ ሆኖ ተገኝቷል።
የሜቴክ የቦርድ ሊቀመንበርነትን ከአቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ከወሰዱ አንድ አመት ያላስቆጠሩት አቶ ደመቀ መኮንን የተነሱበትም ምክንያት አልታወቀም።

No comments:

Post a Comment