Tuesday, February 27, 2018

የፊታችን ሐሙስ የተጠራው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ተራዘመ።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የኢሕአዴግን ሊቀመንበር ለመምረጥና ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነውን ግለሰብ ለመወሰን እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል። በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች በተለይም በሕወሃትና በኦሕዴድ መካከል ያለው ፍጥጫ ለስብሰባው መራዘም ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ታምኖበታል። ከእያንዳንዱ አባል ፓርቲ 45 በአጠቃላይ 180 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ምትክ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርን ለመምረጥ ስብሰባ የተጠራው ለፊታችን ሀሙስ የካቲት 22/2010 ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የሚመረጠው የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አርብ በተጠራው የፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ እንደሚሰየም የተጠበቀ ቢሆንም ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ስብሰባው ተራዝሟል። ለአንድ ሳምንት የተገፋውና እንደገና ለቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ መርሃ ግብር የተያዘለት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በተለመደው አሰራር በስራ አስፈጻሚው በቀረቡለት ሶስት እጩዎች ላይ ድምጽ መስጠት ይጠበቀበት ነበር፡ አዲስ ፎርቹን ከአዲስ አበባ እንደዘገበው። ሆኖም ይህንን የተለመደ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ የማያስችል ሁኔታ በመፈጠሩ በድርጅቱ የ29 አመታት ታሪክ ድምጽ እስኪሰጥ ድረስ የሚመረጠው ሰው የማይታወቅበት ሁኔታ ተከስቷል። እንደከዚህ ቀደሙ በሚቀርቡት እጩዎችም ሆነ በሚመረጠው ግለሰብ ላይ በኢሕአዴግ ደረጃ ስምምነት ባለመኖሩ ለሊቀመንበርነቱ ሶስት ሰዎች ከፊት መስመር ላይ መቆማቸው
ተመልክቷል። የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ )ዶክተር አብይ አህመድን በእጩነት ያቀረበ ሲሆን፣ የብአዴኑ አቶ ደመቀ መኮንንም ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል።ከደቡብ ክልል ደኢሕዴን መጀመሪያ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን ከመረጠ በኋላ ዘግይቶ በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንደቀየራቸውም ታውቋል። አቶ ሽፈራው ሽጉጤም ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ሕወሃት እጩ እንዳላቀረበም ተመልክቷል።ሆኖም በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች ከአቶ ደመቀ መኮንንና ከአቶ ሽፈራው ሽጉጤ አንዱን ለመውሰድና ለማስመረጥ በመካከላቸው ልዩነት እንደተፈጠረ የተሰማ ሲሆን ዶክተር አብይ እንዳይመረጡ ግን የሕወሃት አመራር መወሰኑንም ምንጮች ገልጸዋል። የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ ባያቀርቡም በአዲሱ ካቢኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ስፍራ ለመውሰድ መወሰናቸውንም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መወሰኑም ተመልክቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ፓርላማው በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ላይ ድምጽ ለመስጠት የፊታችን አርብ የያዘው ቀጠሮ እንደተጠበቀ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።ከየአባል ፓርቲዎቹ 15 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ በጉዳዩ ላይ ለመምከር ለነገ ስብሰባ እንደተጠራም ታዉቋል።በስብሰባው ላይ ስምምነት ካልተደረሰም የፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባም ሊራዘም እንደሚችል ታምኖበታል።

No comments:

Post a Comment