Monday, February 5, 2018

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አራቱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ አመራሮች ለ2ተኛ ጊዜ ተፈረደባቸው።

ተከሳሾቹ በድጋሚ የ6 ወራት እስራት የተፈረደባቸው በችሎት ውስጥ በዳኛው ከመቀመጫቸው እንዲነሱ ታዘው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው ተብሏል። ጠበቆቻቸው ግን እኛ ከተነሳን ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም ነበር ሲሉ ውሳኔውን ተቃውመውታል። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ያሉትን ተከሳሾች አቶ በቀለ ገርባ፣ደጀኔ ጣፋ፣አዲሱ ቡላላና ጉርሜሳ አያኖ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባለመነሳታቸው ችሎት ደፍረዋል ተብለዋል። በዚሁም መሰረት በአራቱም ተከሳሶች ላይ የ6 ወራት የእስር ቅጣት በድጋሚ ተላልፎባቸዋል። ከዚህ ቀደምም በችሎት ውስጥ ዘመሩ ተብሎ ችሎት በመድፈር ወንጀል ለ6 ወራት እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸው እንደነበር አይዘነጋም። ተከሳሾቹ በአሁኑ ችሎት “ባለፈው በመናገራችን ተቀጥተናል”በሚል ከመቀመጫቸው እንዳልተነሱ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ተናግረዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን በችሎት ውስጥ በሚጠሩበት ወቅት እጃቸውን ቢያወጡም ፍርድ ቤቱ ካልተነሱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስላላከበሩ ርምጃ እወስዳለሁ በማለት የ6 ወራት እስራት ቀጥቷቸዋል። ተከሳሾቹ ለፍርድ ተቀጥረው ችሎት በመድፈር ቅጣት የተጣለባቸው ያለ አግባብ መሆኑን ጠበቆቻቸው ተናግረዋል። በችሎቱ ፊት እኛ ከተነሳን ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም በሚል ጠበቆቻቸው ውሳኔውን መቃወማቸው ተሰምቷል። በችሎት መድፈር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የተፈረደባቸው አራቱ የኦፌኮ አመራሮች በሁሉም ላይ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 28/2010 መቀጠሩንም ለማወቅ ተችሏል።

No comments:

Post a Comment