Monday, February 5, 2018

በአማራ ክልል በዚህ ዓመት የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎትን ከ10 በላይ ለሚሆኑ ከተሞችና ቀበሌዎች ለማዳረስ በሚል የተመደበው 445 ሚሊየን ብር በሕወሃት በመዘረፉ አገልግሎቱን ማግኘት እንደማይችሉ ተገለፀ ፡፡



በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ከሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ማለትም ከአገልግሎት ፥ ከአዲስ መስመር ዝርጋታ ጥያቄዎች ፥ ከቅጣትና ከልዩ ልዩ ገቢዎች የሰበሰበው 445 ሚሊዮን ብር ለትግራይ ክልል መሰጠቱ ታውቋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሰሜን ምዕራብ ሪጅን የስድስት ወር የስራ ክንውን ሲገመገም በዚህ ዓመት በአማራ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ እቅድ ተይዞላቸው የነበሩ 10 ከተሞች ምንም እንቅስቃሴ አልተደረገላቸውም። ጉዳዩን አስመልክቶ የሕዝብ ማመልከቻ በተደጋጋሚ ሲቀርብ ምላሽ በመጥፋቱ አንዳንድ ሰዎች የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኃላፊውን አጥበቀው ሲጠይቁት ” በደብረፅዮን ትዕዛዝ 445 ሚሊየን ብር ወጭ ሆኖ ወደ መቀሌ አካውንት እደገባ እና በዚያ ለልማት ስራ ይውላል ” የሚል ምላሽ ከአሁኗ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አዜብ ምላሽ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል ፡፡ የኢሳት የመረጃ ምንጭ እንዳመለከተው ኢንጂነር አዜብ ለሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኃላፊው በሕወሃት የተወሰደው ገንዘብ ሊመለስ እንደማይችል አረጋግጠውላቸዋል። እናም ስራው እንዲሰራ ከተፈለገ ገንዘቡን ከሕዝብ እንደገና እንዲሰበስብ ማዘዛቸው ነው የተነገረው። በዚህ መሰረት በሪጅኑ አዲስ መስመር እንዲገባላቸው ከጠየቁና ከተመዘገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገንዘቡ
ከሕዝብ የቆጣሪ ክፍያ እንዲሰበሰብ አዘዋል። እናም ቀደም ሲል በኪሎዋት 40 ብር የነበረው 90 ብር እንዲከፈል እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ዋጋን አለመክፈል እና የመሳሰሉት ሲከሰቱ አንድ ደንበኛ ይቀጣ የነበረው 36 ብር ወደ 150 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል ተብሏል። በተጨማሪም ለአዲስ መስመር ጠያቂዎች የግምት ክፍያ ከነበረው በላይ በእጥፍ እንዲከፍሉ በማድረግ ገቢያቸውን በማሳደግ ገንዘቡን እዲሰበስቡ እና ለታቀደው ስራ እንዲያውሉ ትዕዛዝ ተላልፏል። ከዚህም ሌላ ይህ አሰራር በቀጣይ እየታየ በቋሚነት እንደሚቀጥልም እንደተነገራቸው ነው ምንጮቹ ያረጋገጡት። በዚሁም ሳቢያ በሪጂኑ ሰራተኞች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥራል ፡፡ ቀደም ሲልም በ2008 በአማራ ክልል በሚገኙ የእርሻ እና ማኑፋክቸሪግ ስራዎች ለተሰማሩ ባላሃብቶች ለብድር አገልግሎት የሚውል 4 ቢሊዮን ብር ከልማት ባንክ አማራ ቅርንጫፍ በአማራ ክልል ስም ወጭ ተደርጎ ለትግራይ ክልል ተሰቷል። በዚህ ምክንያት በአማራ ክልል በተጠቀሰው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለኪሳራ ተዳርገው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ብድር ተከልክለው በአራጣ እና ከብአዴን ብድርና ቁጠባ ተቋም በከፍተኛ ወለድ ተበድረው መኖሪያ ቤታቸውን የሸጡ እና የታሰሩ እንዳሉ ይታወቃል ፡፡ ይህን ጉዳይ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ስብሰባ ላይ “አደሕይቶ መግዛት ነው፣ ለአንድ ክልል በአደላ መልኩ እንዲህ እየደጎሙ መደገፍ እጅግ አሳፋሪ እና ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው” በማለት አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቷል። በወቅቱ የብአዴን ስራ አስፈጻሚው አቶ በረከት ስምዖን የተጠቀሰው 4 ቢሊዮን ብር ከአማራ ክልል ተወስዶ ለትግራይ ክልል እንደተሰጠ አምነው የተሰጠበት ምክንያትም “በአማራ ክልል ፕሮጀክት ቀርፆ የሚያቀርብ ባለመኖሩ በወቅቱ የተሻለ አፈፃፀም የነበረው የትግራይ ክልል ስለነበር ገንዘቡ ወዲዚያ ሊዛወር ችሏል ” ማለታቸው ይታወሳል ፡፡

No comments:

Post a Comment