Tuesday, February 20, 2018

እንግሊዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ እንደሳዘናት ገለጸች

የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ “ ወዳጃችን እና አጋራችን ኢትዮጵያ አሳሳቢ በሆነ ጊዜ ላይ ትገኛለች” ብሎአል። ስርዓት ባለው መልኩ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አወንታዊ ቢሆንም፣ ይህንን ጥረት የሚያበላሽ ፣ አሳሳቢና አሳዛኝ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል ሲል በአዋጁ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልጽ አድርጓል። አዋጁ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ እና ለውጭ አገር ባለሀብቶች ተስፋ የሚያስቆርጥ መልእክት የሚሰድ መሆኑን የገለጸው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ፣ አዋጁ ጊዜ አጭር እንዲሆን እንዲሁም እስካሁን የተደረጉ ለውጦችንም መልሶ የሚንድ እንዳይሆን ተስፋ እናደርጋለን ሲል አክሏል። የሰብአዊ መብቶቸና ህገ መንግስቱ እንዲከበር ፣ ሰዎችን በስፋት የማሰር እንቅስቃሴ እንዲገታና የተጣለው የኢንተርኔት እገዳም እንዲነሳ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጠይቋል። መንግስት ፈጣን፣ ግልጽ፣ ሰላማዊ እና ህገመንግስቱን በጠበቀ ሁኔታ አዲስ አመራር እንዲሰይምና ይህም አመራር የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዲቀጥል እድል እንዲሰጠው መስሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። የአሜሪካ መንግስት እና የአውሮፓ ህብረተም እንዲሁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አጥብቀው ተቃውመዋል። አዋጁ በአገሪቱ እያሽቆለቆለ ያለውን ኢኮኖሚ ይበልጥ የሚጎዳው መሆኑን በመግለጫው ጠቅሰዋል። ምዕራባውያን አገራት አዋጁን እየተቃወሙት ቢሆንም፣ የአገዛዙ ባለስልጣናት አዋጁ አገር ለማረጋጋትና የንብረት መውደምን ለመከላከል አስፈላጊ በመሆኑ እንገፋበታለን የሚል መግለጫ እየሰጡ ነው።

No comments:

Post a Comment