Monday, February 5, 2018

ለ61 ወታደራዊ መኮንኖች የተሰጠው ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ በሰራዊቱ ውስጥ ያለውን ብሶትና ምሬት ለማዳፈን ያለመ ነው ተባለ።

ፋይል ኢሳት ያነጋገራቸው ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሙያዎች እንደገለጹት ያለዕውቀትና የውጊያ ልምድ በብሄር ኮታ የታደለው ወታደራዊ ማዕረግ የሃገሪቱን ኢኮኖሚም ሆነ የመከላከያ ሰራዊት አቅምን ከግምት ያላስገባ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። ባለፈው ዓርብ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሃት የሚመራው መንግስት 4 የሙሉ ጄነራል፣ የ3ሌተናል ጄነራል፣ የ14 ሜጀር ጄነራልና የ40 ብርጋዴየር ጄነራል ማዕረግ መስጠቱ ይታወሳል። በቀደሙት የኢትዮጵያ መንግስታት ዘመን ለ60 ዓመታት ኢትዮጵያ ሙሉ ጄኔራል አልነበራትም። ባለፈው ዓርብ በፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የተሰጠው የማዕረግ እድገት ኢትዮጵያን የ5ሙሉ ጄኔራሎች ባለቤት የሚያደርጋት ሆኖ ተመዝግቧል። አሁን በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ አንድ ጄኔራል በትምህርትና በልምድ የሚጠበቅበትን ደረጃ ሳያሟላ ማዕረግ መሰጠቱ ለወታደራዊ ባለሙያዎች አስገራሚ ጉዳይ ሆኖባቸዋል። ወታደራዊ አካዳሚ በመግባት አስፈላጊ የሆነውን ዕውቀት ሳያገኙ፣ በውጊያም ሆነ በአጠቃላይ ወታደራዊ ክህሎት በቂ ልምድና አቅም ላይ ሳይደርሱ የሙሉ ጄነራልነት የተሰጣቸው መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎች ዓለምዓቀፍ
መስፈርትን ጨርሶ ያልጠበቀ አሳፋሪ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲሉ ይገልጹታል። በመከላከያ ሚኒስቴር የጥናትና ምርምር መምሪያ የቀድሞ ሃላፊ ኮሎኔል ደረሰ ተክሌ እንደሚሉት የማዕረግ እድገቱ የትኛውንም ወታደራዊ መመዘኛ በትንሹ እንኳን ማሟላት ያልቻለ ነው። ከትምህርት አንጻር አብዛኞቹ ጄኔራሎች ከዘጠነኛ ክፍል ያልዘዘለ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በዝርዝር የገለጹት ኮሎኔል ደረሰ ተክሌ የብሄር ኮታ ለማመጣጠን በሚል ከሀገሪቱ የመከላከያና የኢኮኖሚ አቅም የማይመጣጠን የጄኔራሎች ሹመት መሰጠቱን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ አየር ሃይል የቀድሞ አብራሪና የበረራ መምህር ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ በበኩላቸው በትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ቁጥጥር ስር የሚገኘው መከላከያ ሰራዊት በጄነራሎች ሹመት እንዲንበሸበሽ የተደረገው የህዝብ ድጋፍ የነጠፈበት አገዛዝ በሰራዊት ጉልበት የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ከሚል ዓላማ እንደሆነ ይገልጻሉ። ለተሾሙት ጄነራሎች የሚሆን መዋቅር በሌለበት ሁኔታ ያለስልጣን ማዕረግ መስጠት ትርጉም የለውም ብለዋል። ጋዜጣና ደብዳቤ ሲያመላልስ ለነበረ ወታደራዊ መኮንን የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ የተሰጠበትን አጋጣሚ ያስታወሱት ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያላሟላ፣ የብሄር ተዋጽዖን ብቻ የጠበቀ፣ የትምህርትና የውጊያ ልምድ ለሌላቸው መኮንኖች በዘፈቀደ የታደለ ማዕረግ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። ሁለቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሙያዎች እንደሚሉት የማዕረግ እድገቱ በሰራዊቱ ውስጥ የተበራከተውን ብሶትና ምሬት ለማስተንፈስ የታለመ ነው። ሆኖም ሰራዊቱ በዚህ እንደማይዘናጋ በመጥቀስ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከህዝብ አብራክ የወጣው ሰራዊት ለሌላ ዙር የጭቆና አገዛዝ እየተዘጋጀ ያለውን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራውን አገዛዝ የሚታገልበት ጊዜው አሁን መሆኑን በመረዳት ከህዝብ ጎን እንዲሰለፍ ሁለቱም ባለሙያዎች ጥሪ አድርገዋል።

No comments:

Post a Comment