Monday, February 26, 2018

የዋልድባ መነኮሳት በእስር ቤት የሚደርስባቸውን በደል አስመልክቶ ለፍርድ ቤት በደብዳቤ አሳወቁ

ታሪካዊው የዋልድባ ገዳም ይዞታችን አይነካ ማለታቸውን ተከትሎ ከዋልድባ ገዳም ተይዘው በማእከላዊና በተለያዩ እስር ቤቶች ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው የቆዩት መነኮሳት የደረሰባቸውን ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በደብዳቤ አሳውቀዋል። በጻፉት ደብዳቤ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰቶች በዝርዝር አቅርበዋል። መነኩሳቱ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት መነኮሳት እንደመሆናችን ሃይማኖታችን የሚያስገድደንን የራሳችን አልባሳት አስኬማ እንጠቀማለን። ይህን አልባሳታችን የምናወልቀው ስንሞት ብቻ ነው። ይህን አልባሳታችንን እንድንለውጥ መገደድ ማለት እምነታችንን እንድንሽር፣ በእግዚያብሔር ስም የተሰጠንን ክብር እንዲዋረድ ማድረግ እንደሆነ ይሰማናል። በመሆኑም የእምነት ልብሳችንን ከምንቀይር የስጋ ሞታችንን እንደምንመርጥ ለእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች በተደጋጋሚ ገልጸናል። ይሁን እንጅ የእስር ቤቱ አስተዳደር መጀመርያ ላይ ተቃውሟችንን የተቀበለ የመሰለ በመሆኑ በእኛ በኩል ለዚህ ፍርድ ቤት አቅርበን የነበረውን አቤቱታ ሳንገፋበት ቀርተናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የእስር ቤቱ አስተዳደር አልባሳቱን እንድናወልቅ ከፍተኛ ጫና እያደረገብን ከመሆኑም በላይ ለከፍተኛ እንግልትና መዋረድ ተዳርገናል። 5ኛ ተከሳሽ አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖት የደረሰባቸውን ሰቆቃ በዝርዝር ሲገልጹ ”ወደዚህ ፍርድ ቤት ለመምጣት የእምነት ልብሴን እንዳወልቅ ስጠየቅ አላወልቅም በማለቴ ማዕረጋቸውንና የአባታቸውን
ስም ያላወኳቸው የደህንነትና ጥበቃ ኃላፊ መሆናቸው የሚታወቁ ገ/እግዚያብሔር የተባሉ የእስር ቤቱ ኃላፊ እያዩና እራሳቸውም እያገዙ ተፈሪ የተባለ ወታደር የጎማ ዱላ በመያዝ ወደ አንድ ሰዋራ ቦታ ሊወስደኝ ሲሞክር መሰሶ ላይ ተጠምጥሜ እምቢ ብልም ልብሴን ከላየ ላይ ለመግፈፍ በኃይል እየጎተተ ያንገላታኝ ከመሆኑም በላይ አቅም አጥቼ ከመሬት ወድቄ ከእነ ልብሴ መሬት ላይ ሲጎትተኝ በሌሎች ሃይ ባይነት የከፋ ጉዳት ሳይደርስብኝ ተርፌያለሁ። ያም ቢሆን በእምነቴ መፅናቴ እንደ ጥፋት ተቆጥሮብኝ ለአንድ ወር ያህል መቀጣጫ በሆነው ዞን 5 በከፋ ሁኔታ እንድቆይ ተደርጌያለሁ።”’ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት አባ ገብረእየሱስ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ”እኔ አባ ገብረእየሱስ ኪዳነማርያም በተመሳሳይ ችግር እየደረሰብኝ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ ሁለታችንም ተለዋጭ ልብስ እንዳይገባልን ተከልክለን በላያችን ላይ ያለው ልብስ በእጅጉ ቆሽሾ በጤናችን ላይ ችግር እያስከተለ ይገኛል። በሌላ በኩል 4ኛ ተከሳሽ በአሁኑ ጊዜ ፈፅሞ ባለወኩት ምክንያትና ለምን ያህል ጊዜም እንደምቆይ ባለወኩበት ሁኔታ በቅጣት መልክ ዞን 5 እንድቆይ ተደርጌያለሁ። ይህ ቦታ ጥፋት ፈፅሟል የሚባል እስረኛ በቅጣት መልክ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ የሚደረግበት እጅግ አደገኛና ለከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የሚዳርግ መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ ነው።” በተከሰስንበት ጉዳይ ይህ ፍርድ ቤት ሊሰጥ የሚችለው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ አስቀድሞ በእስር ቤት እየደረሰብን ያለው በደል ግን እምነታችንን የሚያዋርድ፣ ስብዕናችንን የሚነካ በመሆኑ ይህ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ያቀረብነውን አቤቱታ ጭምር በማየት የአገሪቱ ሕገ መንግስት ለሃይማኖት ነፃነት የሰጠውን ጥበቃ መሰረት በማድረግ በደል የፈፀሙብን የእስር ቤቱ ሰራተኞችና ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድልን እንዲሁም በእስር ቤቱ አስተዳደር ላይም መብታችን የሚያስከብር ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እናመለክታለን። ሲሉ በፊርማቸው የተደገፈ የአቤቱታ ደብዳቤያቸውን አስገብተዋል። በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ሰላማዊ እስረኞች የተወሰኑት ቢፈቱም የዋልድባ መነኮሳት፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ወጣት ዮናታን ተስፋዬ፣ አቶ ብስራት አቢ፣ መኳንንት ካሳሁን፣ የመሳሰሉ አያሌ እስረኞች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment