Friday, February 2, 2018

በኤርትራውያንና በአፍጋኒስታውያን መካከል በተነሳ ግጭት በርካታ ሰዎች ቆሰሉ

በፈረንሳይ የወደብ ከተማ ካሌይ በኤርትራውያንና በአፍጋኒስታውያን መካከል በተነሳ ግጭት በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ታወቀ።
የጦር መሳሪያ ድንጋይና የብረት ዱላ በጨመረውና ትላንት በተከሰተው በዚህ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች መጎዳታቸው የተገለጸ ሲሆን ቢያንስ አራቱ በጥይት መቁሰላቸውም ተመልክቷል።
ግጭቱ ከአካባቢው የፖሊስ ሃይል በላይ በመሆኑ ተጨማሪ የፈረንሳይ የፖሊስ ሃይል ወደ አካባቢው መሰማራቱም ታውቋል።
በፈረንሳይ የወደብ ከተማ ካሌይ ትላንት የተከሰተው ግጭት መነሻ በትክክል ያልታወቀ ቢሆንም ለስደተኞቹ የሚሰጠውን የምግብ እደላ ተከትሎ ግጭቱ መቀስቀሱ ይፋ ይሆኗል።

ቢቢሲ በግጭቱ በትንሹ 5 ሰዎች መሞታቸውን ቢዘግብም የፈረንሳዩ የዜና ምንጭ ፍራንስ 24ን ጨምሮ በፈረንሳይ የሚገኙ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ግን በግጭቱ የሞተ ሰው አለመኖሩን ገልጸዋል።
ነገር ግን ከጉዳተኞቹ ውስጥ አንዱ በአስጊ ሁኔታ ላይ መሆኑን አስፍረዋል።
ኤርትራውያኑ በብዛት ዱላ ይዘው የሚታዩበት ምስል በስፋት እየተሰራጨ ሲሆን አፍጋኒስታውያኑ የጦር መሳሪያ ያገኙበት ሁኔታ ግን አነጋጋሪ ሆኗል።
ከተጎዱት 20 ያህል ሰዎች ውስጥ እድሜያቸው ከ16 እስከ 18 የሆኑ አራት ኤርትራውያን ለህክምና ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል።
ስደተኞቹ በወደብ ከተማዋ የሚገኙት የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጌራርድ ኮለምቦ ዛሬ ባወጡት መግለጫ ሁኔታውን ለመገምገም አርብ ምሽት ከፓሪስ ወደ ካሌብ እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።
በግጭቱ በአፍጋኒስታውያኑና በኤርትራውያኑ ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር ጸጥታ በማስከበር ላይ የነበሩ የፈረንሳይ ፖሊሶችም መጎዳታቸው ታውቋል።

No comments:

Post a Comment