Tuesday, February 20, 2018

የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ከአንድ አምባገነን ወደ ሌላ አምባገነን አገዛዝ መሸጋገር አለመሆኑን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት የምንታገልለት ለውጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል። በለውጡ ሂደት ስልጣን ሃላፊነት በሌላቸው እጅ እንዳይገባ በከፍተኛ የሃላፊነትና የአጣዳፊነት ሁኔታ መታገል አለብን ሲሉም ገልጸዋል። ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ የወቅቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ለብሔራዊ እርቅ ደንታ እንደሌለው በአሁኑ ጊዜ የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አመላካች ነው ብለዋል። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቀባይነት የሌለውና እንደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የሚቆጠር ነው ባይ ናቸው።–የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ። እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ከአንድ አምባገነን ወደ
ሌላ አምባገነን አገዛዝ መሸጋገር አይደለም። እናም ሕዝቡ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይሰብረዋል ነው ያሉት። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በቪዲዮ በተለቀቀ መልዕክታቸው እንዳሉት የሕወሃት ኢሕአዴግ አገዛዝ እየተፍረከረከና እያከተመለት መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ባሉ አባል ድርጅቶች የለውጥ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች መፈጠር መጀመራቸው፣ የትግሉ ውጤት ስኬታማ መሆኑን እንደሚያመለክትም ገልጸዋል። በዚህ የለውጥ ሂደት ወገኖቻችን የታሰሩበት፣የተገረፉበትና የተገደሉበት ትግል ሃላፊነት በሌላቸው ሃይሎች እጅ እንዳይገባም ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል ብለዋል። እናም የምንታገልለት ለውጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይሁንታ ባገኘበት ሁኔታ የሽግግር መንግስት የሚፈጥር መሆን አለበትም ነው ያሉት።ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዋናው የትግል ስልታችን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ነው ሲሉም ገልጸዋል። በዚሁ ትግል ታዲያ በኑሮ ውድነት እየተንገላታ ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብም ዝምታውን ሰብሮ ትግሉን እንዲቀላቀል ጠይቀዋል። ለመከላከያ፣ለኢሕአዴግ አባላትና ለትግራይ ሕዝብም አገዛዙ እያከተመለት በመሆኑ ከአገዛዙ መደበቂያነት ወጥተው የሕዝቡን ትግል እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

No comments:

Post a Comment