Friday, August 5, 2016

ሶስት የኢሲኤ (ECA) ሰራተኞች ታሰሩ

ኢሳት (ሃምሌ 29 ፥ 2008)

አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት  መንግስታት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ ቦምብ እና መሳሪያ ተገኝቷል በሚል ሶስት የድርጅቱ ሰራተኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ። ዋና ሃላፊው ሚስተር ካርሎስ ሎፔዝ  የድርጅቱን ሰራተኞች ባልተጣራ ጉዳይ አሳልፈው መስጠታቸው በሰራተኞች ዘንድ እያነጋገረ መምጣቱንም መረዳት ተችሏል።
አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታተ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽ/ቤት ግቢ ወስጥ ተገኘ ከተባለው መሳሪያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ሚኪያስ ቸርነት፥መላኩ ቡልቶ፣ እና ፋንታሁን ገድሉ መሆናቸውም ታውቋል።

ሶስቱ ኢትዮጵያውያ ሃሙስ  ተይዘው ሲወሰዱ የጽ/ቤቱ ዋና ሃላፊ ሚስተር ካርሎስ ሎፔዝ ተባባሪ መሆናቸውም ተመልክቷል። በአንዳንድ የድርጅቱ ሰራተኞች በተለይም በኢትዮጵያውያኑ  ዘንድ ድርጊቱ  በኢትዮጵያ መንግስት የተቀነባበረ ነው የሚል ጥርጣሬ መኖሩንም የኢሳት ምንጮች ከአዲስ አበባ  ገልጸዋል።
የጽ/ቤቱ ዋና ሃላፊ ሚስተር ካርሎስ ሎፔዝ ከአንጋፋው የህወሃት ታጋይ እና የቀድሞው አዲስ አበባ ከንቲባ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ጋር ባላቸው ቅርበት የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር  መለስ ዜናዊ ፕሮቶኮል ሹም የነበሩትን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የሕወሓት አባላት በድርጅቱ ውስጥ መቀጠራቸውም ተመልክቷል።
ከእነዚህ  ግለስቦች ውስጥ ከፊሉ በአቶ ጌታቸው አሰፋ ለሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት በተደራቢነት እንደሚሰሩ በአንዳንድ ሰራትኞች ዘንድ መታመኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች የታሰሩት ሰራተኞች ከእነዚህ ጋር በተቀነባበረ ሁኔታ ሰለባ ሳይሆኑ እንዳልቀሩም ያስረዳሉ።

No comments:

Post a Comment