Friday, August 19, 2016

የአዲስ አበባ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ እሁድ የሚካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ አስመልክቶ መግለጫ አወጣ

ኢሳት (ነሃሴ 13 ፥ 20108)
የአዲስ አበባ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ በቀጣይ እሁድ በአብዮት አደባባይ ለሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ህዝቡ በነቂስ እንዲወጣ ጥሪ አቀረበ። 
ኮሚቴው ነሃሴ 13 ቀን 2008 ዓም ባወጣው መግለጫ፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተቀጣጠለ ባለ ህዝባዊ እምቢተኝነት ውስጥ እንደምትገኝ፣ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ700 በላይ ወገኖቻችን መገደላቸው፣ በ10ሺዎች ለእስር እንግልትና መሰወር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። 

የአዲስ አበባ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴው በመግለጫው የአዲስ አበባ ህዝብ በወገኖቹ ላይ የሚፈጸመውን ግድያ እስራትና አፈና በንዴት እና ቁጭት ውስጥ እንደከተተው፣ የሚሞተው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አገር እንደሆነ፣ ይህንንም ማስቆም ካልተቻለ የሃገር አንድነት እና የጋራ ሰላማዊ ኑሮ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል አመላክቷል።
የአዲስ አበባ ህዝብ እንደሰው የመኖር ያለመኖር የህልውና ጥያቄ ከፊቱ ተጋርጦበታል የሚለው መግለጫ ኢትዮጵያ ከሌለች አዲስ አበባ የለችም፣ ኢትዮጵያ ከፈረሰች አዲስ አበባም ትፈርሳለች በማለት አስጠንቅቋል። በመሆኑም ሃገራችን ብሎም አዲስ አበባ ከገጠሟት ፈተና ለመውጣት በጋራ መነሳትና ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ማቀጣጠል ጊዜ የሚሰጠው እንዳልሆነ አመላክቷል። መግለጫውን አስከትሎም የአዲስ አበባ ህዝብ የሚያቀጣጥለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ለዘመናት የተጠራቀመ መከራና ስቃዩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያሰናብትበት ብቻ ሳይሆን በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ቀጣይ ህይወታችን ዋስትና የምናረጋግጥበት ነው በማለት አስገንዝቧል።
የአዲስ አበባ ህዝባዊ እምቢተኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ባወጣው በዚህ መግለጫ የህወሃት ጠባብና ጨቋኝ አገዛዝ አዲስ አበባን በቁጥጥሩ ስር በማዋል የከተማዋን ነባር ነዋሪዎች ከቀያቸው በማፈናቀል ለከፍተኛ እንግልት ዳርጓቸዋል በማለት ይገልጻል። የአዲስ አበባ ነዋሪ በከተማ ረሃብ ተመቷል የሚለው መግለጫ ህዝቡ ከቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ትርፍራፊ እየፈለገ የሚበላበት አንገት የሚያስፈፋ ደረጃ ላይ ደርሰናል በማለት ይገልጻል።
የአዲስ አበባ ህዝብ ከፊት ለፊቱ የተጋረጠበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን የሚዘረዝረው ይህ መግለጫ፣ እነዚህ ችግሮች የሚቀረፉት የስርዓት ለውጥ በማምጣት መሆኑን ይገልጻል። በመሆኑም በኦሮሚያ፣ በአማራ እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተቀጣጠልውው ህዝባዊ እምቢተኝነት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment