Wednesday, August 17, 2016

ህወሃት/ኢህአዴግ በአምስት ከተሞች ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ አቅዷል ተባለ

ኢሳት (ነሃሴ 11 ፥ 2008)
ህወሃት የሚመራው መንግስት የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ በማሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ትላልቅ ከተሞች የሽብር አደጋ በማድረስ በአልሸባብ ላይ ለማላከክ ማቀዱን ተገለጸ።
የሽብር ጥቃት እንዲደርስባቸው በህወሃት አመራር የተመረጡ ከተሞች አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ጎንደር፣ ባህርዳርና፣ ሻሸማኔ መሆናቸው ተነግሯል። በተጨማሪም ህወሃት በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማቀዱን ለኢሳት ከደረሰውና ለህዝብ ይፋ ከሆነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። 
ህወሃት/ኢህአዴግ ሶማሊኛ ተናጋሪ የሆኑትን የሶማሌ ክልል ተውላጆችን ወደተጠቀሱት ከተሞች በማምጣት በህዝቡ ላይ ጥቃት ለመፈፀም እንዳቀደ የተናገሩት የኢሳት ምንጮች፣ ይህ የሽብር ጥቃት በጸረሽብር ጦርነት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው አቋም አለም አቀፍ ድጋፍ ያስገኝልኛል ብሎ እንደሚያስብ ለማወቅ ተችሏል። በከተሞች ላይ የህወሃት አመራር ሊወስደው ያሰበው ጥቃት በአገር ውስጥ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በጸረሽብር ህግ መሰረት ለማስቆም ይረዳል ብለው እንደሚያስብ ተነግሯል። 

“በህዝብ ላይ ጥቃት ከመፈጸም ለምን ሌላ አማራጭ አንፈልግም?” ብለው የጠየቁ የአማራና ኦሮሞ ብሄር ተወላጅ የሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ በህወሃት ሃይሎች ታፍነው ወዴት እንደተወሰዱ ለማወቅ አለመቻሉ ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ አልሸባብ የቀጣናው የፀጥታ ሥጋት መሆኑ እንደጨመረና የሽብር ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችል ማሳሰቡን ሪፖርተር ረቡዕ ባወጣው ዘገባ ገልጿል።
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት እየሆነ መጥቷል ያለው የኢጋድ ሪፖርት፣ ‹‹አልሸባብ የሶማሊያ የፀጥታ ሥጋት ብቻ አይደለም፡፡ በመሆኑም አካባቢያዊ የተቀናጀ ምላሽ ይጠይቃል›› ማለቱን ሪፖርተር በዘገባው አስፍርሯል።
አሁን ኢጋድ ያወጣውን ሪፖርት በማስመልከት ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የፖለቲካ ተንታኝ እንደገለጹት፣ በኦሮሚያና አማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቀልበስ ህወሃት እየወሰደ ያለውን ሃይል የተሞላበት እርምጃ ድጋፍ ለመስጠት ሆን ብሎ የተሰራ ድራማ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒነት ስለሌለው ሊወስደው ያሰበውን የሃይል እርምጃ በኢጋድ በኩል እያስነገረ ነው ሲሉ እነዚህ ተንታኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
የህወሃት አመራር በከተሞች ላይ ጥቃት መፈጸሙ አይቀርም ያሉት ስማቸው እንዲነገር ያልፈለጉ የፖለቲካ ተንታኞች፣ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ኢትዮጵያ መሆኗን ተገን በማድረግ ጥቃቱን በአልሻባብ እንደተፈጸመ ለማስመሰል ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት እንደታሰበ ታውቋል።
ህወሃት መራሹ መንግስት ከዚህ በፊትም በአዲስ አበባ ሶስት ቦታ ቦምብ በማንፈዳት ኤርትራንና የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን መውቀሱን ዊኪሊክስ የአሜሪካ ኤምባሲን ጠቅሶ መዘገቡን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment