Wednesday, August 3, 2016

በርካታ ኢትዮጵያውያን በግጭት ከምትታመሰው ደቡብ ሱዳን መውጫን አጥተው እንደሚገኙ ገለጹ

ኢሳት (ሃምሌ 27 ፥ 2008)
ነዋሪነታቸው በጎረቤት ደቡብ ሱዳን የሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ በመዛመት ላይ ካለው ግጭት መውጫን አጥተው እንደሚገኙና ከመንግስት ምላሽ ማጣታቸው ለኢሳት አስታወቁ። 
ከመዲናይቱ ጁባ በቅርብ ርቀት ላይ በመካሄድ ያለው ግጭት ወደ ዋና ከተማዋ ይዛመታል በሚል የተለያዩ ሃገራት ዜጎቻቸውን ከደቡብ ሱዳን እያስወጡ መሆናቸው ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በሃገሪቱ ዳግም በተቀሰቀሰው ግጭት ከ60 ሺ በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው በመፈናቀል ጎረቤት ዩጋንዳ በመሰደድ ላይ መሆናቸውን አመልክቷል። 

ነዋሪነታቸውን በጁባ የሆነ ኢትዮጵያውያን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ከሃገሪቱ ሊወጡ አለመቻላቸውንና ግጭቱ ለደህንነታቸው ስጋት እየሆነ መምጣቱን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ጁባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለማነጋገር ሙከራን ቢያደርጉም አምባሳደሩ ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
የሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያና ሌሎች ሃገራት ግጭቱ ሊባባስ ይችላል በሚል ስጋት ስላደረባቸው ዜጎቻቸውን ከሃገሪቱ በተሽከርካሪ በማስወጣት ላይ መሆናቸውን የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጁባ ከተማ በመንግስትና በአማጺ ወታደሮች መካከል የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ አሜሪካና የተለያዩ ሃገራት በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢምባሲዎች ልዑካናቸውን ማስወጣታቸው ይታወሳል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ማክሰኞ ስድስት የአማጺ ቡድን ሚኒስትሮችን ከሃላፊነት ማስነሳታቸው ግጭቱ ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋትን ያሳደረ ሲሆን፣ እስከ ሰኞ ድረስ ብቻ 60 ሺ ሰዎች ወደ ዩጋንዳ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ሃላፊ የሆኑት ስቴፋን ኦ’ብርያን ደቡብ ሱዳን ወደ ከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ልትገባ ትችላለች ሲሉ ማሳሰባቸውን አልጀዚራ ቴለቪዥን ዘግቧል።
በሃገሪቱ ከቀናት በፊት ጉብኝትን ያደረጉት ሃላፊው በደቡብ ሱዳን ዳግም የተቀሰቀሰውን ግጭት የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግስትና በአማጺ ቡድን ወታደሮች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑንና ውጊያው በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት መጠኑን እያሰፋ ሊሄድ እንደሚችል ስጋት ማሳደሩን ከሃገሪቱ ሪፖርትን ያቀረበው ቴሌቪዥን ጣቢያው አመልክቷል።
ከሃገሪቱ መውጫን አጥተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መንግስታችሁ ነው ጣልቃ እየገባ ግጭት ያመጣብን በማለት ዛቻ እያደረሱብን ነው ሲሉ ለኢሳት አስታውቀዋል።
በደቡብ ሱዳን ከ30 ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በንግድና በተለያዩ የግል ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ታውቋል።
በሃገሪቱ መውጫን አጥተው ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።

No comments:

Post a Comment