Wednesday, August 17, 2016

በደብረማርቆስ የተጀመረው አድማ ረቡዕ እንደቀጠለ ነው

ኢሳት (ነሃሴ 11 ፥ 2008)
ማክሰኞች ከሰዓት በኋላ በደብረ ማርቆስ ከተማ የተጀመረው የሰራ ማቆም አድማ ረቡዕ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉንና ነዋሪው የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ እንዲያበቃ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ። 
የከተማዋ ነዋሪ ያነሱት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸው ይታወሳል። 
ተቃውሞ ረቡዕ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉን የተናገሩት እማኞች በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም የግል ድርጅቶች በአድማው ተሳታፊ መሆናቸውን ከዜና ዝግጅት ክፍላችን ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች አስረድተዋል። 
የከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈው ቅዳሜ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን በማድረግ በጎንደር እና ባህር ዳር ከተሞች እንዲሁም በኦሮሞያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎችን ማውገዛቸው ይታወሳል። 


ይሁንና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ለመበተን በወሰዱት እርምጃ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ድርጊቱ ቁጣ መቀስቀሱን እማኞች አስታውቀዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ህዝቡ ያነሳው ጥያቄ ምላሽ እስኪገኝ ድረስ የጀመሩት የስራ ማቆም አድማ ቀጣይ እንደሚሆን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ የደብረማርቆስ ነዋሪዎች አክለው አስረድተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በግል ተነሳሽነት እያካሄዱ ያለውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከከተማዋ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ስራቸው መስተጓጎሉ ታውቋል።
በቅርቡ በጎንደርና ባህር ዳር ከተሞች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎችን በመቃወም የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ለሶስት ቀናት ከቤት ያለመውጣት አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ለሶስት ቀናት ብቻ በወሰዱት የሃይል እርምጃ፣ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የፓርቲ አመራሮችና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።

No comments:

Post a Comment