Wednesday, August 3, 2016

የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቶበታል ሲሉ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ

ኢሳት (ሃምሌ 27 ፥ 2008)
የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ከተመለሰ ዓመታት አልፈውታል ሲሉ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ። ዛሬ ጥያቄውን የሚያነሱ የሌሎች ሃይሎች እጅ ስላረፈበት ነው ሲሉም የመንግስት ያሉትን አቋማቸውን ገልጸዋል። የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር እና የብዓዴን አመራር አባል አቶ ካሳ ተክለብርሃንም ወልቃይት በትግራይ ክልል የተከለለው ነዋሪዎቹ ትግሬዎች በመሆናቸው ነው ሲሉ ዕርምጃው ትክክል ነበር ሲሉ ማጠናከሪያ ሰጥተዋል። 

ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቀን በባህርዳር ሲከበር ከውጭ ሃገር ከመጡ ኢትዮጵያውያንና በዝግጅቱ ከታደሙ በሃገር ቤት ከሚኖሩ ዜጎች ጋር በተደረገ ውይይት የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ በተለያዩ ሰዎች የተነሳ ሲሆን አሳሳቢ መሆኑም ተመልክቷል።
ከሃምሌ 25 - 27 ፥ 208 በባህርዳር በተካሄደው በሁለተኛው የዳያስፖራ ቀን ለማንነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ ጎንደር የተከሰተው ሁኔታ አያጋጥምም ያሉት ተሰብሳቢዎች የወልቃይት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አሳስበዋል።
ሪፖርተር የጠቀሳቸው አቶ በላይ ታከለ እና ወ/ሮ ጸጋ ስላሴ የተባሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች የወልቃይት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ በጎንደር ውስጥ ያለው ጸጥታ እንደሚያሳስባቸው አመልክተዋል። “ጎንደር እንደ ጎንደር መቀጠሏም ያሳስበኛል” ማለታቸው ተመልክቷል።
ከተሰብሳቢዎቹ የተነሳውን ስጋትና ጥያቄ ወደጎን የገፉት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጉዳዩ ምላሽ ካገኘ አመታት ተቆጥረዋል በማለት ሲናገሩ የፌዴራል ጉዳዮች ሚንስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንም የአቶ ሃይለማርያምን ሃሳብ በማጠናከር ወልቃይት የትግራይ ክልል አካል መሆኑ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
በወልቃይት የማንነት ጥያቄና በአጠቃላይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን የህወሃት የበላይነት በተመለከተ ብአዴን ውስጥ እየጎለበተ ያለውን ተቃውሞ ለማዳፈን ከሚንቀሳቀሱ የብዓዴን አመራሮች ግንባር ቀደሙ አቶ ካሳ ተክለብርሃን መሆናቸው እየተገለጸ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment