Friday, August 5, 2016

በእነብርሃኑ ተክለ ያሬድ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 4 ተከሳሾች እስራት ተበየነባቸው

ኢሳት (ሃምሌ 29 ፥ 2008)

ባለፈው አመት ወደ ኤርትራ በመጓዝ የግንቦት ሰባት ሃይልን ለመቀላቀል ሙከራ ሲያደርጉ በድንበር ላይ ተይዘዋል ተብለው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው አራት ተከሳሾች ከአራት እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።
ተከሳሽ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ የግንቦት ሰባት አባል በመሆንንና አባላትን በመመልከል አድርጎታል በተባለው ክስ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአምስት አመት ጽኑ እስራት ተወስኖበታል።

በተመሳሳይ ክስ ስር የነበሩትና የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ወ/ት እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማሪያም አስማማውን እና አቶ ደሴ ካህሳይ ደግሞ እያንዳንዳቸው በአራት አመትና በአምስት ወር ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ተከሳሾቹ የፍርድ ሂደታቸው እየተካሄደ ባለበት ወቅት ድርጊቱን እንደፈጸሙ ለችሎት ማመናቸው ይታወሳል።
አራቱ ተከሳሾች በሃገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ አማርጮች በመጥፋታቸው ምክንያት ድርጊቱን አምነውንበት እንደፈጸሙት ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸውም ይታወቃል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የእስር ቅጣቱ ሊተላለፍባቸው መቻሉን በውሳኔው አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment