Thursday, August 18, 2016

ተመድ በኢትዮጵያ የተፈጸመውን ግድያ የማጣራት ጥያቄ የልማት ኣጋሮች እንዲደግፉት ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ

ኢሳት (ነሃሴ 12 ፥ 2008)
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ያቀረበውን ጥሪ የሃገሪቱ የልማት አጋሮች እንዲደግፉት ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ። 
የሃገሪቱ የልማት አጋሮች የድርሻቸውን ተጽዕኖ ማሳደር ይኖርባቸው ሲል የገለጸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ድርጊቱ መንግስት ያለተጠያቂነት ሰላማዊ ሰልፈኞችን መግደል እንደማይችል ጠንካራ መልዕክትን የሚያስተላልፍ ነው ሲሉ አስታውቋል። 

የልማት አጋሮች የሚወስዱት እርምጃ ለመንግስት ከሚያስተላልፈው መልዕክት በተጨማሪ ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው ለፍትህ እያቀረቡ ያለው ጥያቄ እየተሰማ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ሂውማን ራይትስ ዎች በወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በቅርቡ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችንና የጅምላ እስራት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት መጠየቁ ይታወሳል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ለቀረበለት ጥያቄ እንደማይተባበር የገለጸ ሲሆን፣ የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት ግድያው በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበትና ድርጊቱን የፈጸሙትም ለፍትህ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆንር የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች አሁን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት አዲስ የአጋርነት አካሄድና ስልትን መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አለም አቀፍ ተቋማቱ መንግስት ለፈጸመው ግድያ ተጠያቂ እንዲሆን እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ካላደረጉ ድርጊቱ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል ሂውማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ አስፍሯል።
በኦሮሚያ ክልል ለወራት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞና በቅርቡ በአማራ ክልል በተፈጸሙ ግድያዎች በአጠቃላይ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ምዕራብያውያን ሃገራትና አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ በመቃወም ለመንግስት በሚሰጡት ድጋፍ ላይ የማስተካከያ እርምጃን እንዲወስዱ አቋሙ በሚገልጽበት ርዕሰ አንቀጽ መጠየቁ ይታወሳል።
ጋዜጣው የያዘውን አቋም ተከትሎ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ተመሳሳይ ጥሪን እያቀረቡ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment