Thursday, July 10, 2014

አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊ ነው !!!

ወንድሙን ሲገሉት ፣ ወንድሙን ካልከፋው፣

ሱሬውን አምጡለት፣ ደሙ እንዲገለማው።



በጉን በጉ በላው በድዱ ጎትቶ ፣

ለማን አቤት ይሏል፣ ሰሚስ የት ተገኝቶ።



የሕዝብ ግጥም

አንዳርጋቸው በሁለት ወንጀለኛ መንግሥታት ትብብር ታፈነ፣ ተወሰደ ፣ ታሰረ ፣ ተሰቃየ።
ይህ አሳዛኝና የሚያበሳጭ ዜና ነው። በዚህ ቅጥፈት በሞላበት ዓለም ውስጥ ሕዝባቸውን በየቀኑ የሚያስሩ፣ የሚገድሉ፣ የሚያፍኑ መንግሥታት ቢተባበሩ ምንም የሚገርም ጉዳይ አይሆንም። አንዱ የሌላውን  እከክ ማከኩ የተለመደ ነው። ይህ የመጀመሪያ ሳይሆን የተደጋገመ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝና የአካባቢው ወንጀለኛ መንግሥታት የተለመደ ወንጀል ነው። ወያኔ ገና ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንዲሁም ከዚያ በፊት ጀምሮ ያስራል ፣ ይገድላል ፣ ያሰቃያል።

በዚህ ሰሞን በተፈጸመው ግፍ ውስጥ አንዳንድ የሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የማነበው ሆነ የምሰማው አንድ በጣም መስተካከል ያለበት አስገራሚ ሃሳብ አለ። “አንዳርጋቸው እንግሊዛዊ ስለሆነ የመኖች አስረው ለወያኔ ማስተላለፍ አይችሉም“ የሚል ንግግርም ይሁን ጽሁፍ አንዳንዴ ብቅ ይላል።  እግሊዛዊነቱስ እሺ ኢትዮጵያዊስ ቢሆን? ይችላሉ ማለት ነው? ለማስፈታት በምናደርገው ጥረት ማናቸውንም መንገድ መጠቀም ይገባ ይሆናል። ግን ደግሞ ዓላማችንን አዘናጊ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ጎጂ ሊሆን አይገባም።


ለመሆኑ ዜግነታችን ምንድነው?

በአንድ ወቅት ከአንድ ጓደኛ ጋር ከሲዊዘርላንድ ወደ ጀርመን በባቡር ስንጓዝ ነበር ። በባቡሩ ባዝል የሚባል የጀርመን ግዛት ሲደርስ የጀርመን ፖሊሶች ገቡና ባቡሩ ውስጥ የተሳፈሩትን ነጮች ማንንም ሳይጠይቁ እኛ ጋ መጥተው መታወቂያ ጠየቁ። እኔ የስደተኛ ፓስፖርቴን ሰጠሁ ። ጓደኛዬ ጀርመናዊ ሆኖ ነበርና የጀርመንን ፓስፖርት ሰጠ። የእኔን ትንሽ ተመልክቶ መለሰልኝ። ጓደኛዬን ግን አብጠርጥሮ ጠየቀው። የጓደኛዬን ብስጭት ሳይ  ሳቄ መጣ ። ሳቄ ደግሞ ምክንያት ነበረው ።



ጓደኛዬ ዜግነቱን የቀየረበት ምክንያት ቪዛ ሳይጠየቅ በአውሮፓና በአሜሪካ እንደፈለገ መንደላቀቅ ስለሚችል መሆኑን ብዙ ጊዜ ሲያወራ ሰምቼው ነበር። ያ የተንደላቀቀበት የጀርመን ዜግነት ፓስፖርት መታወቂያ ሳይሆን መጠየቂያ ሆነበት። ።ከዜግነት የሚያገኘው የቪዛ ጥቅም እንኳን በጥቁርነቱ ተሸፈነ። እሱ በጥያቄ ተንገፍግፎ እኔ ግን በስደተኛ መታወቂዬ በሰላም ታለፍኩ። ይህ ቁጥጥር በባቡሩ ላይ ጥሩ ውይይት አጫረ። ጀርመኖች በተከፋፈለ ሁኔታ ሰለ ጀርመንነት. ስለ ስደተኝነት ፤ እሱንም ተከትሎ ስለሚደረገው ወንጀል እንደ ተዐምር ተወራ። እኛም ዘረኞች ብለን ተሳደብን፣ እነሱም በጥቁር ጀርመንነታችን አሹፈው ተሳለቁብን።



ታዲያ ይህ መከረኛ ጓደኛዬ የባድሜ ጦርነት ጊዜ ኤርትራ ውስጥ ነበር። ጦርነቱ ሲነሳ እንደ ማንኛውም ጀርመን ወደ ጀርመን ኤምባሲ ሄዶ አመለከተ። ለጀርመን ዜጎች አውሮፕላን እንደሚመጣ ተነገረው። ጠበቀ ። በኩራትም ለዘመዶቹ ሁሉ ጉራውን ነዛ። አውሮፕላኑም መጣ። ነጭ ጀርመኖችን ጫነ፤ ከዛም ነጭ አውሮፓውያንን ቀጠለ፣ አውሮፕላኑ ሞላ . . .  ሁለት  ሴትጥቁር ጀርመኖችን ብቻ ጭኖ ሌሎቹን ጥሎ ሄደ ። ጓደኛዬ ጭንቅላቱን ቀብሮ ፣  በእፍረት ወደ ዘመዶቹ ተመለሰ። በሌላ አውሮፕላን ተሳፍሮ ግብጽ ደረሰ። ካይሮ ጀርመን ኤምባሲ ሄዶ እርዳታ ጠየቀ። ማንም ግን የረዳው የለም።



ሌላው 1997 ምርጫ መጭበርበር ምክንያት በተነሳው አመጽ ምክንያት አንድ የማይረባ አሜሪካዊ የሆነ ዜጋችን ፣ ቅንጅትን በጣም ሲወቅስ ነበር ይባላል። “እኛ አሜሪካውያንን ወደ ሃገራችን ሳንመለስ ቅንጅቶች አመጹን ስላስነሱ ይጠየቃሉ። እኛ አሜሪካኖችን አደጋ ላይ መጣል ነው።“ ብሎ ሲመጻደቅ እንደነበር ድፍን የልደታ ሰው የሚያውቀው ነው። የእኛ “አሜሪካዊ“ ስለ አንዲት በቁም ለሞተች ነፍሱ መዳኛ መፈለጉ መሆኑ ነው።



የጀርመን ዜግነት ወይም የሌሎች ዜግነትን መውስድ ልዩነቱ ቪዛ ሳይጠየቁ ብዙ ሃገሮች ከመግባት በላይ አይጠቅምም። እሱም መቼም ከእከክልኝ ልከክልህ ፖለቲካ አካባቢ እስካልደረስን ነው። ሰሞኑን የሚታየው ይህ ነው። የእንግሊዝ መንግሥት የአንዳርጋቸውን መታሰር ምክንያት በማድረግ ጦርም አልመዘዘም፣ ማዕቀብም አልጣለ፣ የረባም መግለጫ አላወጣም። ለይስሙላ ከንፈር ከመምጠጥ በላይ ምንም አላደረገም። እኛ ግን እራሳችን በፈጠርነው ዜና “እንግሊዛዊ ስለሆነ ወያኔ ይፈታዋል“ እያልን ተዘናግተን ማዘናጋት አያስፈልገንም። ይህ ከብዙ የተፈጸሙ ሁኔታዎች አለመማር ነው። ምዕራብያውያን ከጥቅማቸው እንጂ እንደ ፕሮፖጋንዳቸው ለዴሞክራሲ የሚታገሉ አለመሆናቸውን ብዙ መረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።



አንዳርጋቸው . . .  የዘረኛ ገዳይ  መንግሥት ተቃዋሚ እንጂ የእከኩልኝ ልከክላችሁ ፓለቲካ ደጋፊ አይደለም። አንዳርጋቸው ጦር አሰልፎ ለምዕራብያውያን ጥቅም እንደ ወያኔ የሚቆም አይደለም። አንዳርጋቸው የምዕራብያውያን ጥቅም ለማስጠበቅ ቀን ከሌሊት የሚሰራም አይደለም። አንዳርጋቸው ለሱዳን ለም መሬት፣ ለጅቡቲ ውሃ፣ ለየመን ትንባሆ ፋብሪካ የሚሰጥ አይደለም።  ስለሆነም እንግሊዝም ሆነ ምዕራብያውያን ቦታ ባይሰጡት የሚጠበቅ እንጂ ያልተለመደ ተግባባራቸው አይደለም።



1997 ምርጫ የንፁሃን ደም እንደ ጎርፍ ሲወርድ አላየንም ፣ አልሰማንም ያሉ  ምዕራብያውያን አሁን ይሰማሉ ብለን ማመን አይኖርብንም። እንዳልሰሙ፣ እንዳላወቁ አውቀው የተኙን ምዕራብያውያን አንድ ጊዜ ይሰሙ ይሆናል ብለን መጠበቅ መቆም አለበት። የእከክልኝ ልከክልህ አለምአቀፋዊ እንቅስቃሴ አባል ሃገሮች ኤምባሲ በራፍ ላይ ቆመን ጮኸን ተመልሰን እቤታችን ቁጭ ብለን ውጤት መጠበቁ መቆም አለበት።



ምዕራብያውያን ሁላችንም አንዳርጋቸው ስንሆን ብቻ ነው የሚሰሙን ማንነታችንን የሚረዱት። ተግባራዊ የሆነ ወያኔን አስፈሪ የሆነ እንቅስቃሴ ስናደርግ ብቻ ነው ካለሰልፍ የኛን ማንነት የሚያውቁት፣ ኤምባሲያቸው ሳንሄድ የሚሰሙን።  ጎበዝ መጃጃሉን እናቁም። ከእባብ እንቁላል እርግብ አይገኝምና ጉልበት አድካሚ የኤምባሲ ሰልፍ እናቁምና በተለየ መንገድ እንደራጅ። ያኔ ነው ድምጽም ኃይልም ልንሆን የምንችለው።



ራዕይ ያለው ትግል፣ ክፍፍል ላይ ያላተኮረ ትግል ዉጤቱ አመርቂ ነው። ይህ የአንዳርጋቸው መታሠር የፈጠረውን የአንድነት መንፈስ መጠቀም ብልህነት ነው። ትግሉ ከድርጅት ጥቅም ባሻገር ሊሄድ ይገባል። ከድርጅት ጋር ብቻ ካስተሳሰርነው ግን ወያኔ ወደሚፈለገው ክፍፍል፣ ወይም ከኤምባሲ ሰልፍ የማያልፍ ትግል ብቻ ሆኖ ይቀራል። ዛሬ ነው መዘየድ።



በዚህ አጋጣሚ የት ሄዱ የሃገር ሽማግሌዎች? የት ሄዱ ምሁራን? የት ሄዱ የፖለቲካ መሪዎች? ዛሬ በዚህ አዋራጅ ወቅት  ፈር ቀዳጅ የሆነ መንገድ ማሳየት ካልቻሉ ምኑ ላይ ነው ሽማግሌነቱ? ፣ ምኑ ላይ ምሁራንነቱ?  ምኑ ላይ የፖለቲካ መሪነቱ ? ውስጥ ለውስጥ ንግግሩ ሊጀመር ይገባል።



የሃያ ሦስት ዓመቱን ትግል ዞር ብለን ተመልክተን የወደፊት መንገዳችንን ካላስተካከልን የመን አይደለም አውሮፓና አሜሪካ መጥተው ቢያንጠለጥሉን ማንም ምንም አይላቸውም። የምንሰለፍላቸውም ምዕራብያውያን ምንም አያደርጉም ። እኛ ብቻ ነን ለእኛ መታገል የምንችለው።



ዜግነታችን አሁንም ቢሆን ወደፊት ኢትዮጵያውነት ነው። ሊያኮራን የሚችለውና በእኩልነት ልንታይበት የምንችለው በኢትዮጵያውነታችን ነው። ጀርመናዊነት ሆን እንግሊዛዊነት ወይም አሜርካዊነት ነጻ አያወጣንም።  ራሳችን ነጻ የምናወጣው ራሳችንን ነን።



ስለዚህም ነው ዜግነታችን ምንድነው? ብለን መጠየቅ ያለብን ዛሬ ነው ። ምዕራብያውያን ባወጡልን መሥፈር ዜግነታችን ለመመደብ ስንሞክር ውርደት ቀለባችን ይሆናል። ቅኝ ገዥዎች እኛን ለመከፋፈል የተጠቀሙበትን መንገድ ለመጠቀም ስንሞክር እነሱም ይንቁናል ። እኛም እንዋረዳለን።  ወያኔ ደግሞ ዜግነታችንን እያዋረደ፣ የሃገርን ጥቅም እየቸበቸበ፣ በጸረ ሽብርተኝነት ስም የጎረቤት ሃገሮች ቡድን እያቋቋመ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በየመን የደረሰብንን በደል ታሪክ ጽፎት ይቀመጣል።



አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊ ነው ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገል ሰው ነው። ምንም ወንጀል የለበትምና ሊፈታ ይገባል። እንግሊዛዊ ስለሆነ አይደለም መፈታት ያለበት። ምንም ወንጀል ስለሌለበት ነው መፈታት ያለበት። ካለምነም ቅድመ ሁኔታ ነው መፈታት ያለበት። እሱ ብቻ አይደለም ሁሉም በወያኔ ስም እየወጣላቸው የታሰሩ የነጻነት ታጋዮች  መፈታት አለባቸው። ይህ ትግል መሪዎችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጰያን ሕዝብ ከወያኔ ዘረኛ አፓርታይድ እስር ቤት ማስፈታት አለበት። “መሪዎቻችን ይፈቱ“ የሚለውን መፈክር ትተን “ወያኔ ይወገድ“ የሚለውን ትግል ማጠናከር ነው መፍትሄው።



ጎበዝ ጠላቶቻችንን ብዙዎች ናቸው። ምሥጢራችን በየአደባባዩ መገኘት የለበትም። የብዙ ንጹሃን ደም በእኛ ጥፋት ሊፈስ ይችላልና  ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ዛሬ ከአንዳርጋቸው ብዙ እንማራለለን። ከትላንትናዎቹ ባለመማራችን ደግሞ የመጣውን ችግርም ማጥናት ያስፈልጋል።



ለማጠቃለል ያህል የኩርዶች መሪን  አብደላ ኦጀላንን ማስታወስ ያስፈልጋል። አብደላ ኦጀላን በሶሪያ ውስጥ ይኖር ነበር ። የቱርክ መንግሥት አብደላ ኦጀላን ከሶርያ ካልወጣ ሶርያን  እወራለሁ ብሎ መስፈራራት ይጀምራል። የሶሪያ መንግሥት ሁኔታውን አይቶ አብደላን ከሃገሩ ያስወጣል። አብደላ ኦጀላንን የሚቀበለው ሦስተኛ ሃገር ያጣል። በመጨረሻም ኬንያ ውስጥ በቱርክ የስለላ ድርጅት ይያዝና ወደ ቱርክ ተወስዶ አንድ ደሴት ላይ ብቻውን ታስሮ ይገኛል። በዛ ወቅት አንድ የኩርድ ተወላጅ የነበረ ጓደኛዬ የነገረኝ ትዝ ይለኛል። ኦጀላን በኩርዶች መሃል ፣ በራሱ ሕዝብ መሃል ቢሆን ኖሮ ይህ አይደርስበትም ነው ያለኝ።



ከዚህ ትልቅ አባባል መማር ያስፈልጋል። መደበቂያችን ፣ የምንታገልለት ሕዝብ ነውና ትግላችንን ሕዝባችን ውስጥ ማድረግ ይኖርብናል። ከሕዝባችን ውጭ ማንንም ማመን አይኖርብንም። ሕዝብ መሃል አዲስ አበባም ጫካ ነች። ሕዝባችን ላይ እምነት ካለን፣ ሕዝባችንም ለዚህ ለዘረኛ ከፋፋይ መንግሥት  አሳልፎ አይሰጠንም።





ለሕዝብ ሲታገሉ በወያኔ እስር ቤት ስለሚሰቃዩ የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ።

(በልጅግ ዓሊ)



No comments:

Post a Comment