Saturday, July 19, 2014

የዛሬ ዕለት፣ በተወሰነ ደረጃ ሰኔ 1 1997 ዓ.ም መሰለኝ (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ)

የተከበረው የፖሊስ ሙያ ሳይንስ ያገኙትን መደብደብ ነው እንዴ!)

ዛሬ ረፋድ ላይ ከቤቴ ስወጣ፣ የምወደውን የዮጋ ስፖርት ሰርቼ እና አምላኬን አመስግኜ ነበር፡፡ ደስ የሚል ጥሩ ስሜትም ነበረኝ፡፡ ታላቁ አንዋር መስኪድ ከደረስኩ በኋላ የተፈጠረውን አሳዛኝ፣ ሰቅጣጭና ዘግናኝ ሁኔታ ከተመለከትኩኝ በኋላ ግን እስከአሁኗ ደቂቃ ድረስ እጅግ ተከፋሁ፤ ብዙ ነገሮች በአዕምሮዬ ተመላሰለሁ፡፡ ከምንም በላይ የሀገሬ አብዛኛው ህዝብ የተጎሳቀለ ሕይወት እና ይህቺ ሃብታም ሆና በብዙ ችግሮች የሚማቅቁ ዜጎችን የያዘች ሀገሬ አሳዘነችኝ፡፡ ኤልያስ ገብሩ
በጣም ሰላማዊ የሆነ ኃይማኖታዊ ሥርዓት በደቂቃዎች ውስጥ ወዳልታሰበ ብጥብጥ እና ረብሻ ውስጥ ሲገባ በዓይኔ ብሌን ስመለከት እንዴት አልከፋ?! በፖሊስ ፊት የተገኙ ዜጎች በሚያሳቅቅ መልኩ የዱላ በትር ሲያርፍባቸው መመልከት እንዴት አያም?! ፖሊስ ሮጦ የደረሰበትን ሰው አናት አናቱን በዱላ ከመታው በኋላ የምስኪን ወገኖቼ ደም ሲፈስ አይቼ እንዴት የዘወትር ፈገግታዬ እና ሳቄን ላምጣው?

ይህቺን ጽሑፍ እየጻፍኩ እንኳ ልቤ በሀዘን ተሞልቶ አይኖቼ ዕንባ አርግዘዋል – የወገኖቻችን ጭንቅላት ተበርቅሶ ደማቸው እንደውሃ ሲፈስ ስመለከት ሞት ምን ያህል ቅርባችን መሆኑንም ተረዳሁ፡፡ (በሕይወቱ ሙሉ፣ በአጋጣሚ፣ ለሰከንድ እንኳን ደም ተንጠባጥቦ መንገድ ላይ ስመለከት ውስጤ በጣም ስለሚረበሽ ወዲያው ፊቴን አዞራለሁ)
ከምንም በላይ የገረመኝና አንባብያንን ዛሬ መጠየቅ የዳዳኝ የፖሊሳዊ ሳይንስ ሥነ-ምግባር በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ሰዎች እንዲያስረዱኝ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚ ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ምላሹ እንደእባብ አናት አናቱን መደብደም የፖሊስ ሳይንስ ሕግ ነው?
እሺ፣ ነገሮችን ለማረጋጋት ተብሎ ፖሊስ መጠነኛ እርምጃ የመውሰድ አጋጣሚ ተፈጠረበት እንበል (እንበል ነው ያልኩት)፣ ከሰዎች የሰውነት አካላት መካከል በዋነኝነት ተመርጦ መመታት ያለበት አናታቸው ነውን? በዚህ አጋጣሚ ሳይንሱን የሚተነትንልኝ ኢትዮያዊ ፖሊስ ባገኝ ደስ ባለኝ፡፡ ወይም ስለሳይንሱ የሚውቅ ሰው ይንገረኝ፡፡
ሰዎች አናታቸው ተመትቶ ደማቸው ሲፈስስ ተመለከትኩ እንጂ እኔም ብሆን እድሜ በእጄ ያዛኳት ላፕቴፕ እንደተዓምር መከላከያዬ ሆነችኝ እንጂ በዚህ ሰዓት አናቴ ተፈንክቶ አልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ ሁኔታውን ባሰብኩት ቁጥር ይዘገንነኛል – የጋዜጠኝነት ሕይወት ከሞት ጋር የሚያላትም ግዴታ እንዳለበት በጽኑ ባምንም!
ከቀናቶች በፊት አልጀዚራ ቴሌቭዥን በዓለም ላይ በተለያዩ ጊዜያት ከሙያቸው ጋር በተገኛኘ የተገደሉ እና አካላቸው ተጎድቶ በቤታቸው የተቀመጡ ወንድ እና ሴት ጋዜጠኞችን ቃለ-ምልልስ እያደረገ፣ የሞቱትን ደግሞ በፎቶግራፍ እያስደገፈ በማሳየት ሰፊ ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ ያቀረበውን ከሁለት ጓደኞቼ ጋር በቤት ተመልክተናል፡፡ የዛሬው የአንዋር መስኪድ አሰዛኝ ሁነት ታዳሚ መሆኔ በፈተና የተሞላ ሙያዬን ይበልጥ እንድወደው እና እስከመጨረሻው ድረስ በዕናት እንድቆምለት ብርታት ሰጥቶኛል – በኢትዮጵያ ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የሞት ጽዋን የተጎኘጩ እና የተለያዩ ዋጋዎችን የከፈሉ እና በመክፈል ላይ ያሉ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ተበትነው የሚገኙ ጋዜጠኞችን ለአፍታም ሳልዘነጋ!
እንደዛሬው አይነት መሰል ሁኔታ ሰኔ 01 1997 ዓ.ም በዚህቺው በመዲናችን አዲስ አበባ ተመልክተናል፡፡ ያኔ ግን ዱላ ሳይሆን ጥይት ነበር፡፡
ኦ አምላኬ፣ መቼ ይሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ያሉ የወገኖቼ እንግልት እና መከራ የሚያከትመው?!
በመጨረሻ መንግሥታችን ሆይ፣ ‹‹ከሁለት ዓመታት በላይ ያቆጠረውን የሙስሊሙ ማኅበረሰብን የመብት ሰላማዊ ጥያቄ አድምጥ! በጠረጴዛ ዙሪያም ተቀምጣችሁ ተወያዩና ሰላማዊ መፍትሄ ስጥ!›› የሚለው እንደኢትዮያዊ ዜጋ ምክሬ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment