Saturday, July 19, 2014

ጨቋኙ እና አምባገነኑ የወያኔ ቡድን በሴቶች እህቶቻችን ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ (የአብስራ ዳኛቸው)

         ወያኔ በ97ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ አይን ባወጣ ድርቅና ምርጫውን በማጭበርበር በአሸናፊነት ተወጥቻለሁ ብሎ የንፁሁን ህዝብ ድምፅ በመንጠቅ እና ድምፁ የነጠቀውን ህዝብ ያደረገውን ተቋውሞ በመሳርያ ሀይል በመጠቀም የንፁሁን ህዝብ ደም በማፍሰስ እና አካል በማጉደል በማን አለብኝነት ፖርላማውን ለብቻው በመቆጣጠር ህዝቡን ያለ ፍላጎት በግድ ሲገዛ የማህበረሰቡ አንድ አካል የሆኑ ሴቶች እህቶቻችን በወያኔ የደረሰውን እልቂት በመመልከት ከፖለቲካ ትግላቸው የሚሸሹና የሚያቆሙ መስሎ ተሰምቶት ነበር በአንፃሩ ግን ቡዙ ለአላማቸው ፅኑ የሆኑ ሴት ታጋዮች እንዲፈጠሩ መንገድ ከፍቷል።
        ሴቶች እህቶቻችን ተቋውሞአቸዉን ለመግለፅ እና በአለም ማህረሰብ ላይ ስለ ሀገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ለማሳወቅ ያስገደዳቸው ነገር ጨቋኙ የወያኔ ቡድን የሴቶችን መብት በሀገሪቷ ላይ ተንሰራፍቶ ባለው ስርአት እና በስርአቱ አንቀሳቃሾች እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ አይምሮዋቸው ተቀብሎት አምኖ መቀበል ስላቃተው ነው።
        አምባገነኑ የወያኔ ስርአት በሀገሪቱ ላይ ዲሞክራሲን ያለገደብ አስፍኛለው በማለት ሴቶች እህቶቻችን በነፃነት የመናገር ሀሳባቸውን የመግለፅ መብት አላቸው በማለት ሲነገር ይደመጣል ነገር ግን እየተገበረ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው ለዚህም ምስክር የሚሆኑት በአሁኑ ሰአት በወያኔ እስር ቤት ተጥለው ከሚገኙት እንኳን ወጣቷ ጋዜጠኛ እና መምህርት ርዮት ተጠቃሽ ናት።
        ወያኔ እንደሚናገረው ከሆነ ርዮት የታሰረችበት ዋናው ምክንያት እርሱ ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጃቸው ነገር ግን ለሀገር ለህዝብ ነፃነት ከቆሙ ፖርቲዎች ጋር ተባብረሻል በሚል የሀሰት ውንጀላ ነው። ርዮት በጋዜጣ ሙያ ላይ ተሰማርታ እንደምትገኝ ይታወቃል በጋዜጠኝነት ስነምግባር ላይ ደግሞ አንድ ጋዜጠኛ ከህዝብ የሚያገኘው ማንኛውም ሀሳብ እና አቋም ግልፅ በሆነ መንገድ ለሚድያ በማቅረብ የህዝብን ድምፅ ማሰማት ነው ርዮትም የፈፀመችው ይህንኑ ሙያዊ ግዴታዋን ነበር ለዚህም አምባገነኑ የወያኔ ቡድን የሰጠው ምላሽ ቢኖር እርዮትን ወደ እስር ቤት መጣል ነበር።
         በአቋሟ ፅኑ የሆነችው እህታችን ግን እስሩም ሳይበግራት ለህዝብ በላከችው መልእክት ህዝቡ ሰላማዊ ትግሉን ከበፊቱ አጥብቆ መቀጠል እንዳለበት እና በወያኔ ማስፈራሪያ እንዳይበገር አሳስባለች። ከምንም በ ላይ የሚያሳፍረው ወያኔ ርዮት ማሰሩ ሳይሆን ርዮት በሌሎች እስረኞች ላይ በሀሰት እንድትመሰክር እና እሷ ነፃ እንድትወጣ ማባበላቸው ነው በአንፃሩ ደግሞ ርዮት እንደ ወያኔ ባለስልጣናት አይምሮዋን ለሆዳ የሸጠች እንዳልሆነች አሳይታቸዋለች።
        በተመሳሳይ ሁኔታ በቅርቡ በሰማያዊ ፓርቲ ሴት አባላት እና አመራሮች ላይ የደረሰው እስራት እና ጭቆና አምባገነኑ የወያኔ ቡድን ሴቶች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ ምን ያህል እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። እነዚህ ትግል ናፋቂዎች ድምጻቸውን በአደባባይ ማሰማታቸው ለጨቋኙ የወያኔ ቡድን ያላቸውን ተቋውሞ ለመግለፅ እና ህዝቡንም ከዚህ መራራ ህይወት በሰላማዊ ትግል ታግሎ እንዲላቀቅ ለመጠቆም ነበር። ሆኖም ግን ሴት ወጣቶቹ በፖሊስ ታፍሰው እስር ቤት ለመጣል ደቂቃዎች አልፈጀም በሌላ በኩል ግን ወያኔ እራሱ ሰው ሰላማዊ ትግሉን በነፃነት ያለምንም ፍራቻ ማድረግ ይቻላል እያለ ለብቻው በተቆጣጠረው ሚድያ 30 ግዜ ይለፍፋል። ህዝቡንም በውሸት ከአንገት በላይ እየደለለ ድብቅ ተግባሩን ይፈፅማል።
        ትዋቂዋ የነፃነት ታጋይ ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ በነበራት የፖለቲካ አቋም በሀገሯ ላይ በነፃነት መታገል ባለመቻሏ ለእስር መዳረጓ የሚዘነጋ አይደለም። በአንፃሩ ደግሞ ለወያኔ የወገኑ የፓርቲው ደጋፊ የሆኑ ምንም አይነት የትምህርት እውቀት ደረጃ ሳይመዘን አንዳች መስፈርት ሳይቀመጥላቸው የአንድ አካባቢ ሰዎች በመሆናቸው ወይም ከጫካ በመምጣታቸው በስልጣን ላይ ተቀምጠው ለፍተው የተማሩ ሴቶች እህቶቻችንን ዋጋ በማሳጣት በደመ ነፍስ ሀገር ሲያስተዳድሩ ይታያሉ።
        ስለዚህ ይህን ስርአት በመደገፍ ጊዜያዊ ጥቅማችሁ አስጎምጅቷችሁ የህዝቡን ደም የምትመጡ የወያኔ ጭፍሮች ከግዚያዊ ፍርፋሪ ይልቅ የብዙኃኑን የኢትዮጵያ ሴቶችን ድምፅ በማክበር ከሌሎች ሴት ታጋዮች ጋር በመቆም ይህን አምባገነን ቡድን ከመሰረቱ ነቅሎ ለመጣል አብራችሁ መቆም እንዳለባችሁ ልቦናችሁ መገንዘብ አለበት።
             ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ሲስተካከሉ፦
-የሴቶች መብት የሚከበርባት
-ሴቶች በነፃነት ሀሳባቸውን የሚገልፁበት
-ሴቶች ባመኑበት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የሚሳተፍበት እና
-ሴቶች በዘር እና በጎሳ ሳይሆን በትክክለኛ የትምህርት ደረጃቸው ህዝብን የሚያገለግሉበት  
  አትዮጵያን መመስረት ይቻላል

                                   ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

No comments:

Post a Comment