Sunday, July 6, 2014

ከግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ልዩ መግለጫና ተግባሪዊ የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪ ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን!!!

በየጊዜው እየከረረና እየገረረ የመጣው ትግላችን “ሁላችን አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ወደ ተባለ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ይህ ጽሁፍ የዚህን የትግል ምዕራፍ ምንነትና ይዘት በአጭሩ ያብራራል። በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈሩት ዓረፍተ ነገሮች ተነበው የሚታለፉ ሳይሆን በተግባር የሚተረጎሙ ሥራዎች ናቸው።

አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ምን ማለት ነው? አንዳርጋቸው ጽጌ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት በጀግንነት የቆመ፤ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ሲከፍል የነበረና አሁንም እየከፈለ ያለ መሪያችን ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ልክ እንደሱ ትሁት ሆኖም ግን ቆራጥ፤ ሆደ ሰፊ በዚያው ልክ ደግሞ መራር፤ አስተዋይና ብልህ ሆኖም ተግባር ተኮር መሆን ማለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ወያኔን ለማስወገድ መደረግ የሚገባውን እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀ ሰው መሆን ማለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ለአገርና ለትውልድ ቤዛ መሆን ማለት ነው።



ወያኔ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ካተኮረባቸው ምክንያቶች አንዱ የወያኔን የዘር ፓለቲካና ፕሮፖጋንዳ በሚያመክን መልኩ በተግባር ትግል ውስጥ ካሉ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ እና ሌሎች ዘውግ ተኮር ድርጅቶች ጋር ንቅናቄዓችን ተግባራዊ ትብብር ማድረግ የሚችሉበት ደረጃ ድረስ ማቀራረብ የቻለ መሪ መሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ ለወያኔ የጉሮሮ ቁስል የሆነበት ደግሞ ከትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጋር ግንቦት 7 የፈጠረው ጠንካራ ትብብር ነው። ከትህዴን ጋር በመሆን አቶ አንዳርጋቸው ወያኔ በትግራይ ሕዝብ ጀርባ መንጠልጠል እንዳይችል አድርጎታል። እናም አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ከዘረኝነት ፀድቶ መገኘት ማለትም ጭምር ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት በኢትዮጵያዊያን እኩልነት እና እኩል ባለመብትነት ከልብ ማመን እና ለእኩልነት በጽናት መታገል ማለት ነው።

አንዳርጋቸው ጽጌን ለመሆን የግድ የግንቦት 7 አባል መሆንን አይጠየቅም። አንዳርጋቸው ጽጌን ለመሆን ለመልካም ዓላማዎች መሳካት ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀትን እንጂ የግድ ከአንድ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር መወገንን አያሻም። ያም ሆኖ ግን አንዳርጋቸው ጽጌን የሆነ ሰው በጠንካራ ድርጅት የታገዘ ትግል አስፈላጊነት ይረዳል።

በመጨረሻም አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ኦኪሎ ኦኴኝ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ እና እዚህ ዘርዝረን ልንጨርሳቸው የማንችላቸው ጀግኖቻችንን ሁሉ መሆን ማለት ነው።

“የሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ዘመቻ ትኩረቶችን በየጊዜው የምንገልጽ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ በሥራ ላይ መዋል ያለበት የዓለም ዓቀፍ ዘመቻው የመጀመሪያ እርከን ትኩረቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል

የዘመቻው የመጀመሪያው እርከን ትኩረቶች

ይህ የመጀመሪያ እርከን ሶስት ቦታዎች ላይ ያተኩራል፡- የመን፣ ብርታኒያ እና ወያኔ

 የመንን በተመለከተ

የየመን መንግሥት የዓለም ዓቀፍ ህግም ሆነ የየመን የራሷን ህግ በመተላለፍ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል። ከመጀመሪያው ጀምሮ ለየመን መንግሥት የተደረገው ተማጽኖ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። እስካሁንም ድረስ የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸውን ማሠሩና ለወያኔ አሳልፎ መስጠቱ በይፋ አላመነም። እኛ ባለን መረጃ መሠረት በአይሮፕላን ማረፊያው ከማገት ጀምሮ በልዩ በረራ ወደ ኢትዮጵያ እስከ መላክ ድረስ ያለውን የውንብድና ሥራ በየመን በኩል ሆኖ የሠራው ቀጥታ ተጠሪነቱ ለየመን ፕሬዚዳንት የሆነው የስለላ ድርጅት ነው። በዚህም ሳቢያ የየመን መንግሥት ሊቀለበስ የማይችል እና በቀላሉ የማይፋቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል። የየመን መንግሥትና ሕዝብ ይህን እንዲያውቁት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው የተግባር እንቅስቃሴ አካል ነው።

የመንን በተመለከተ የሚቀጥለው ሳምንት ዘመቻችን ግብ ቁጣችንን የየመን ፕሬዚዳንት እና የየመን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የየመን ሕዝብም እንዲያውቅ ማድረግ ነው። የሚከተሉት ተግባራት ለአብነት ያህል ተጠቅሰዋል።

 ለየመን ፕሬዚዳንት አዲስ መረር ያለ ደብዳቤ ተጽፎ በፋክስና በኢሜል በየመን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች አድራሻዎች መላክ። በመልዕክት መጨናነቅ ከሚገባቸው የየመን ተቋማት አንዱ አዲስ አበባ የሚገኘው የየመን ኤምባሲ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆናችሁ በዘመቻው የምትሳተፉ የሕዝብ ስልኮችን እንድትጠቀሙ፤ የኢንተርኔትና የፋክስ መልክቶችን ስትልኩ ራስን ለጉዳት በማያጋልጥ መንገድ መደረግ ይኖርበታል።

 ብርታኒያን በተመለከተ

የእንግሊዝ መንግሥት ማድረግ የነበረበትን እና ማድረግ ይችል የነበረውን ሁሉ አድርጓል ብለን አናምንም። እርምጃው ፈጣን አልነበረም፤ አሁንም አይደለም።

ስለሆነም እንግሊዝን በተመለከተ የዘመቻችን ግብ የእንግሊዝ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈጉ መክሰስ እና ከአሁን በኋላም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለውና መሪያችንን እንዲያስፈታ መወትወት ነው። የሚከተሉት ተግባራት ለአብነት ተዘርዝረዋል።

የእንግሊዝ መንግሥትን በህግ መክሰስ (ይህ በንቅናቄው ጽ/ቤት የሚሠራ ነው)፤

 ወያኔን በተመለከተ

ወያኔን በተመለከተ የሚደረጉ ትግሎች በሙሉ ወያኔን ከስልጣን ማስወገድን ያለሙ መሆን ይኖርባቸዋል። ወያኔም ለመጣል ትልቁን ድርሻ የሚያበረክተው ሕይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ ወገኖቻችን የሚያደርጉት ተግባር ነው፤ እንቀላቀላቸው።

በተለያዩ ምክንያቶች ወሳኙን ትግል መቀላቀል የማይችሉ ወገኖቻችን በያሉበት ሆነው ይህንኑ የሚያግዙ ተግባራት መፈጸም ይኖርባቸዋል። እነዚህ ተግባራት፣ የወያኔ ባለሟሎች በገቡበት እየገቡ በማሳፈር እረፍት በመንሳት፤ የፈፀሟቸውን ወንጀሎች በአደባባይ በመናገር እንዲሸማቀቁ በማድረግ፤ ማንነታቸው ለሸሪኮቻቸው ወይም ለሥራ ባልደረቦቻቸው በመንገር ወዳጅ በማሳጣት፣ ቢዚነሶቻቸው እንዲከስሩ በማድረግ የፋይናንስ አቅማቸውን በማዳከም ረገድ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ ሊጤን ይገባል። ከዚህ አኳያ ሊደረጉ ከሚገቡ ተግባራት የሚከተሉት በምሳሌነት ተዘርዝረዋል።

በየአገሩ በተለያዩ ሽፋኖች ተሰግስገው ያለት ወንጀለኞች የወያኔ ሹማምንትና ደጋፊዎችን ለፍርድ ማቅረብ፤የምዕራብ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግኑኝነት እንዲመረምሩ ማሳሰብ። በወጉ ሳያስተምሩ ለወያኔ ሹማምንቶች ዲግሪ የሚያድሉ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆችን ማስጠንቀቅ፤ ተግባሮቻቸውን ለተማሪዎቻቸው ጭምር መንገር (ለምሳሌ University of Greenwich ከ International Leadership Institute ጋር ያለውን ግኑኝነት እንዲሰርዝ፣ እስከዛሬ የሰጣቸውንም የማስትሬት ዲግሪዎች እንዲመረመር የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፎ በብዛት በፋክስ መላክ፤ ተመሳሳይ ደብዳቤ Open University እና ከወያኔ ጋር ተሻርከው ለሚሠሩ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች መላክ)

በመጨረሻም የወጣቱ የማያልቅ የፈጠራ ችሎታ ከላይ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱ ሆኖም ግን ውጤታማ የሆኑ የተቃውሞ መግለጫ ዘዴዎች ያፈልቃል ብለን እናምናለን። ስለሆነም ዘመቻውን በየአካባቢው በሚገኝ ሀሳብና ፈጠራ ማዳበር ይቻላል።

ይህ ዘመቻ ወያኔን ከስልጣን ለማባረር ምድር ላይ ከምናደርገው የመረረ ትግል ጋር ሲቀናጅ የሚፈለገውን ውጤት ስለሚያስገኝ ለነፃነቱ ግድ ያለው ዜጋ ሁሉ በሙሉ ሃይሉና አቅሙ ተሳትፎ እንዲያደርግ ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራዊ ጥሪ ያቄርባል ::

በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን !!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!


No comments:

Post a Comment