Thursday, April 12, 2018

የወልቃይት ተወላጆች አዲስ ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገለጹ

(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 4፣ 2010ዓም)
የአዲ ረመጥ ወረዳ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪዎች ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዳመለከቱት "የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ትግራይ ቅርንጫፍ" የካቲት 2 ቀን 2010 ዓም አዲስ ክስ እንደቀረበባቸው አመልክተዋል።
“ከወንጀል ሕግ አልፎ በሽብርተኝነት ተከሰው የነበሩ ሰዎች ክሳቸው በተቋረጠበት ሁኔታ በእኛ ላይ አዲስ ክስ መመስረቱ የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄውን እንዳያነሳ በእኛ ለማስፈራራት እና እኛንም ለመበቀል፣ በተለይም የወልቃይት ህዝብ በሰበብ አስባቡ ተበትኖ ከተወለደበት ሀገር ወጥተን ስደተኛ እንድንሆን፣ እኛን እያሰሩ እና እያባረሩ የትግራይን ሕዝብ በእኛ እርሻና ቤት እየተኩ የወልቃይትን ሕዝብ ከስር መሰረቱ ለመንቀል እንደሆነ ከግምት አልፎ እውነትነት እየታየበት ያለ ሁኔታ ላይ ደርሰናል” የሚሉት አስተባባሪዎች፣ ይህንንም በማስረጃ የሚያረጋገጡት እውነታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ በማንነት ጥያቄ ምክንያት እስካሁን የተፈፀመብንን ግፍ አልበቃ ብሎ አሁን በአዲስ መልክ የተጀመረውን የማንነት ጠያቂ ኮሚቴዎችን የማጥቃት ዘመቻ ከእኛ ከተከሳሾቹ አልፎ የወልቃይት አማራ ሕዝብ ስነ ልቦና በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ እና ሕገ መንግስታዊ መብቱን የሚያፍን ኢ_ዲሞክራዊያዊ አካሄድ “ በመሆኑ በቀረበባቸው ክስ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
አስተባባሪዎቹ ሚያዝያ 3/2010 ዓም በጻፉት ደብዳቤ “ የህዝብ አንድነት መንካት” የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ገልጸዋል፤፡
“ ቀደም ብሎ የተከሰሱት የኮሚቴ አባላት ክስ ተቋርጦ መለቀቃቸውን ዓለም አውቆት እያለ አዲስ ምክንያት በመፍጠር "የሕዝብ አንድነት መንካት" በሚል ሌላ ምክንያት መከሰሳችን፣ አንድም የወልቃይት ተወላጆችን በሰበብ አስባቡ ከትውልድ ቀያቸው የማስለቀቅ አላማ ያዘለ ወይንም ደግሞ አሁን እየተፈጠረ ያለውን ሰላም የማይፈልግ አካል “ ሆን ብሎ እየፈጸመው ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment