Monday, April 2, 2018

“ከልባችን ይቅር ተባብለን በብሄራዊ መግባባት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንሻገር” ሲሉ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ተናገሩ

(ኢሳት ዜና ማጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ/ም) አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስታዊ ስልጣኑን ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያውን ከልባቸው ይቅር ተባብለው፣ የትናንትናውን ምዕራፍ ዘግተው በብሄራዊ መግባባት ወደ ቀጣዩ አገራዊ ጉዞ እንዲሸጋገሩ ጥሪ አቅርበዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ይህን እውን ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ቢናገሩም፣ በተጨባጭ ስለሚወስዱት እርምጃ ግን አልገለጹም። ዶ./ር አብይ ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ፓርቲዎች የሚታዩበት መነጸር እንደሚቀየር ተናግረው፣ ፓርቲዎቹ “ እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብለው እንደሚጡ የዜጎች ስብስብ” ይታያሉ ብለዋል። ዶ/ር አብይ በተለያዩ ጊዜዎች መስዋትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞችና በደንብ ሳይቦርቁ ህይወታቸው ለተቀጠፈው ለውጥ ፋላጊ ወጣቶች፣ ለስነ ልቦናና አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብለዋል። የኢትዮጵያን ህዝብም እንደሚክሱ ቃል ገብተዋል። ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ ታሪክ
፣ ለህዝቦቿ አንድነትና ትስስር ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጡም በንግግራቸው ጠቅሰዋል። “ትናንት አባቶቻችን በመተማ፣ አድዋ፣ ማይጨውና ካራማራ አጥንቶቻቸውን ከስክሰው የከበደ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩት አገር አለን ያሉት ዶ/ር አብይ ፣ ይህችንን ውብና አኩሪ ታሪክ ያላት አገር በመረከባችን እድለኞች ነን ሲሉ አክለዋል። የኢትዮጵያውያን ማንነት እንዳይለያይ ሆኖ የተገመደና የተዋሃደ መሆኑን ዶ/ር አብይ የብዙዎችን ቀልብ በሳበ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል። ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ሳይታወቅ በገዳ ስርዓት ዲሞክራሲን ስታራምድ የቆየች አገር መሆኗን የጠቀሱት አዲሱ ጠ/ሚኒስትር፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ ስራዎችን እንደሚሰሩም ገልጸዋል።ኢትዮጵያ የጋራችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምጽ የሚሰማባት ዲሞክራሲን እንመሰርታለን ሲሉ ቃል የገቡት ዶ/ር አብይ፣ “ከዚህ በኃላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የህይወት መስዋዓትነት አያስፈልገንም።የሚያስፈልገን መደማመጥ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል። በውጭ ፖሊሲያቸውም በተለይ ከኤርትራ መንግስት ጋር እርቀ-ሰላም ማውረድ እንደሚሹ በመግለጽ፣ ለኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። ዶ/ር አብይ በንግግራቸው የእናታቸውንና የባለቤታቸውን ሚና በአጠቃላይ ሴቶች አገርን በመለወጥ በኩል የሚኖራቸውን ሚና አጉልተው አሳይተዋል። የዶ/ር አብይን ንግግር በርካታ ኢትዮጵያውያን በመልካም ሁኔታ የተቀበሉት ቢሆንም፣ ቃል የገቡትን ወደ ተግባር ይለውጡት ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ንግግሩን በአድናቆት ከተመለከቱት መካከል ታዋቂው ምሁርና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም አንዱ ናቸው። “ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በግሉ በነጻነት አስቦ በአገር ጉዳይ ቁምነገሮች ላይ እንደዓቢይ አዲስ ነገርና የአስተሳሰብ እንከን የሌለበት ነገር ሲናገሩ አልሰማሁም፤ እኔ የሰማኋቸው ቅጭብጭቦች የዓቢይ ንግግሮች በሙሉ ሰውዬው የማሰብ ችሎታው የጠራ እንደሆነ ያረገጋግጡልኛል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ እንዲህ ያለ ባለሥልጣን ሰምቼ አላውቅም” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው የጻፉት ፕ/ር መስፍን፣ “ በአደባባይ በወያኔዎች ፊት ስለኢትዮጵያ ሕዝብ የተናገረው፣ ስለሥልጣን የተናገረው አዲስና ግሩም ነው” ብለዋል። ዓቢይ “በወያኔ በራስ አለመተማመን ሕመም ላይ በእግሩ ቆመበት” ሲሉም አድናቆታቸውን አክለዋል።

No comments:

Post a Comment