Wednesday, April 18, 2018

በምስራቅ ጎጃም ዞን የመርጦ ለማርያም ከተማ ወጣቶች በአገዛዙ ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ዋሉ

(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓ/ም) ለተቃውሞው መነሻ የሆነው ለድልድይ ስራ የዋለ ትርፍ ብረት በ4 መኪኖች ተጭነው ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዛቸውን የአካባቢው ህዝብ በመቃወሙ ነው። ወጣቶቹ እቃውን የጫኑትን መኪኖች አስቁመው እቃው እንዲራገፍ ሲጠይቁ ከወረዳው ባለስልጣናት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። ባለስልጣኑ ግለሰቦቹ ህጋዊ ፍቃድ እንዳላቸው ገልጸው ለማሳመን ቢሞክሩም ህዝቡ አሻፈረኝ በማለት ውዝግቡ እስከምሽት ቀጥሎአል። ህዝቡ በተቃውሞው በመቀጠሉ እቃው እንዲራገፍ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ የተደሰቱ ወጣቶች ተቃውሟቸውን ሲገልጹ፣ አገዛዙን የሚቃወሙ መፈክሮችንም ሲያሰሙ አምሽተዋል። ነዋሪዎች ፣ ንብረቱ ዘመድኩን የሚባል የህወሃት ሰው እንደሆነ ሲገልጹ፣ አባይ ድልድልይን ከሚጠብቁት ግለሰቦችና ከወረዳው ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ንብረት ለማሸሽ በመሞከሩ ህዝቡን ለቁጣ እንዳስነሳው ገልጸዋል። ሌሎች የቀሩ ብረቶችም እንዳይቀንቀሳቀሱና ብረቶችን ለመውሰድ በሚመጣ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ የከተማዋ ወጣቶች አስጠንቅቀዋል።

No comments:

Post a Comment