Thursday, April 12, 2018

የኢህአዴግ ነባር አመራሮች አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የኢህአዴግን መስመር ያስቀጥላል የሚል እምነት እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው

(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 4፣ 2010ዓም)
ነባሮቹ የኢህአዴግ አመራሮች አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የኢህአዴግን መስመር የማስቀጠል ፍላጎት አለው ብለው እንደማያምኑ እየተናገሩ ነው።
የኢሳት የኢህአዴግ ምንጮች እንደገለጹት ነባር ከሆኑት የኢህአዴግ አመራሮች መካከል አቶ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ጸሃዬ፣ በረከት ስምዖን፣ ህላዊ ዮሴፍ፣ ስዩም መስፍንና ሌሎችም በድርጅቱ ውስጥ የቆዬ አመራሮች አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ኢህአዴግ ከሚመራበት የልማታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ይልቅ ወደ ሊበራል አስተሳሰብ የሚያዘነብል ፖለቲካ የሚከተል፣ የህዝብን ጥያቄ ያለሳይንሳዊ ትንታኔ እፈታለሁ ብሎ ቃል የሚገባና ለመተግበር የሚቸገር እንዲሁም ከኢህአዴግ ድምጽ ይልቅ የተቃዋሚዎችን ድምጽ ለመስማት የፈጠነ ነው በማለት ቅስቀሳ እያደረጉ ነው።
የኢህአዴግ መስመር በጸረ-ህዝቦች መስመር ሲደለዝ አናይም በማለት አዲስ ቅስቀሳ የጀመሩት እነዚህ ነባር አመራሮች፣ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የኢህአዴግን መስመር የማስቀጠል ፍላጎት ከሌለው መስዋትነት የተከፈለበትን ድርጅት ለማዳን እንደሚተጉ እየገለጸ ነው።

በነባሮቹ አመራር የተዋቀረው ቡድን የተለያዩ ደጋፊዎችን ለማሰባሰብ ላይ ታች እያለ ሲሆን፣ የኦሮምያ ክልል አካሄድ በአገራችን መጥፎ ሂደት የፈጠረና አገሪቱን በዘላቂ ችግር ውስጥ የሚከታት ነው በማለት እየተናገሩ ነው። ክልሎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ በሚል ስልጣን የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ከተሰጣቸው ስልጣን አልፈው በሚመሩት ክልል ግጭት በማስነሳት ማእከላዊ ስልጣኑን ለመቆጣጠር የሄዱበት አካሄድ፣ ነገ በሌሎች ክልሎች የሚደገም በመሆኑ ይህ አካሄድ ካሁኑ መገታት አለበት በማለት የሚናገሩት ነባር አመራሮች፣ ዶ/ር አብይ ከኢህአዴግ ፈቃድ ውጭ የስልጣን ሹም ሽር የሚካሂዱ ከሆነ እንዲሁም ከድርጅቱ ፈቃድ ውጭ ከተቃዋሚዎች ጋር በመነጋገር የተቃዋሚዎችን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ ከሆነ፣ ድርጅቱ ህልውናውን ለማስጠበቅ እንዲሁም የሰማዓታቱን አደራ ለመጠበቅ ሲባል ተገቢ ነው የሚለውን እርምጃ ይወስዳል በማለት እያስፈራሩ ነው።
ነባር አመራሮቹ ታዋቂ የሚሉዋቸውን ሰዎች ሳይቀር አስተያየት እየሰበሰቡ ሲሆን፣ ህዝቡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር እውነተኛ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ አመኔታ በመጣሉ፣ በአሁኑ ሰዓት በይፋ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ እንዳደረጋቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል። የኢህአዴግ ጭንቅላት ነን ብለው የሚያስቡት በረከት ስምዖንና አባይ ጸሃዬ ሚናቸው እየተሸረሸረ የመጣ እንደሚመስላቸውና የክሱ ፊት መሪዎች እንደሆኑ ምንጮች ይገልጻሉ።
በፓርላማው የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴም እንዲሁ አሁንም ድረስ የጠ/ሚኒስትሩን መመረጥ በአወንታዊነት እንዳልተቀበሉት ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ከህወሃት “ጊዜ እንስጠው” በሚል ለዘብተኛ አቋም የያዙት አቶ አረከበ እቅባይ መሆናቸው ተነግሯል። ከህወሃትም ከኦህዴድም መሆን አልቻሉም የተባሉት አባዱላ ገመዳም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ በተለይም ኦህዴድ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ዝም ብለው መመልከታቸው በነባር ጓደኞቻቸው እያስተቻቸው ነው።
በነባሩ አመራሮች መካከል ሙሉ በሙሉ አንድ የሚባል አቋም እንደሌለም ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ በረከት፣ አቶ አስመላሽና ህላዊ ዮሴፍን የመሳሰሉት የመለስ ሚና እየተረሳ እና ራዕዩና ስራዎቹም እየተደመሰሱ ነው በማለት ብሶታቸውን ሲገልጹ፣ አቶ አርከበ፣ አቶ ስብሃትና አቶ አባይ በበኩላቸው የመለስ ሌጋሲ አለመነሳቱን ጠቃሚ ነገር አድርገው እያዩት ነው።
በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዙሪያ ህወሃት እንደ ድርጅት አንድ ወጥ አቋም መያዝ የተሳነው ሲሆን፣ ብአዴን እነ አቶ በረከትን ገለል በማድረግ ሙሉ ድጋፉን በአብይ ላይ አሳርፏል። ይሁን እንጅ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የሚያካሂዱት ሹም ሽር የድርጅቶችን አሰላለፍና የግለሰቦችን አቋም ይወስናል በማለት ምንጮች አክለው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment