Wednesday, April 18, 2018

በጉጂ እና በጌዲዮ ብሄረሰቦች መካከል የተጀመረው ግጭት ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል

 (ኢሳት ዜና ሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስደት የዳረገው የሁለቱ ብሄረሰቦቸ ግጭት ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል። በተለይ ባንቆ ጎትቲ 2 የቡና ሳይቶች እንዲሁም በጨልጨል አንድ የቡና ሳይት ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን፣ በቃርጫ ደግሞ ካለፈው ሃሙስ ጀምሮ ከተሰደዱ ህጻናት መካከል ደግሞ የተወሰኑ ህጻናት መሞታቸው ታውቋል። ቆስለው ከነበሩ የጌዲዮ ተወላጆች መካከልም በህክምና እጦር 4 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግጭቱ በተነሳባቸው አካባቢዎች የተገኙ ቢሆንም፣ ግጭቱን ለማስቆም እርምጃ ሲወስዱ አለመታየቱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ከ1987 ዓም ጀምሮ ከድንበር ማካለል ጋር በተያያዘ በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል የተነሳው ግጭት፣ለበርካታ ዜጎች ሞትና ስደት ምክንያት ሆኗል። አርበኞች ግንቦት7 ሆን ተብሎ የተቀሰቀሰውን ግጭት አውግዟል። ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ “ በዚህ ወንጀል እጃቸው ያለበት ሁሉ በህግ ፊት እንዲቀርቡ” ጠይቋል። ንቅናቄው ሚያዝያ 9 ቀን 2010 ዓም በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተወረወረ ቦንብ እና በጭፍን በተተኮሱ ጥይቶች ሳቢያ የዜጎች ሕይወት መጥፋቱንም ኮንኗል።

No comments:

Post a Comment