Thursday, August 2, 2018

የፍቃዱ ተክለማርያም የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

Image may contain: 3 people(ኢሳት ዲሲ--ሐምሌ 26/2010) የአንጋፋው የኪነጥበብ ባለሙያ ፍቃዱ ተክለማርያም የቀብር ስነ ስርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈፀመ።
ከቀብር ስነ ስርዓቱ ቀደም ብሎ በብሔራዊ ትያትር ቤት በርካታ አድናቂዎቹና የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት አስከሬኑ አሰኛኘት ተድርጎለታል።
የአንጋፋው ከያኒ ፍቃዱ ተክለማሪያም የቀብር ስነ ስርዓት አጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አድናቂቆቹ እና የጥበብ ሰዎች በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
ከመንግስት ባለስልጣናት መካከልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቀብር ስነስርአቱ ላይ ተገኝተዋል።
አርቲስት ፈቃዱ በህይወት ዘመኑ ያበረከታቸው በርካታ ስራዎቹና የህይወት ታሪኩ በቀብር ስነ ስርዓቱ ወቅት መነበቡንም ከወጡት መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል።

አርቲስት ፍቃዱ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ አምባሳደር ተደርጎ በተሾመበት ወቅት በርካታ ስራዎች እንዳከናወነ የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሰኞ ዕለት ለጸበል ወደ ወሎ መጓዙንና በዛም ከዚህ አለም በሞት መለየቱ የሚታወስ ነው።
ፍቃዱ አብዛኛውን የዕድሜውን ክፍል በመድረክ ያሳለፈ ሲሆን በርካታ ቲያትሮችንም ተጫውቷል።
በሬዲዮ ድራማዎች፣ በመጽሐፍት ትረካዎች፣ በቴሌዥን ድራማዎች እና በርካታ ፊልሞች ላይ ተሳትፏል።
በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ፍቃዱ ከዚህ እድሜው አብዛኛውን ዘመን በመድረክ ላይ ማሳለፉንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፍቃዱ ከአባቱ ተክለማሪያም ኪዳኔና ከእናቱ ከወይዘሮ እልፍነሽ ወንድሙ በ1948 ነው የተወለደው።
አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ የተወለደው አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም ሚያዚያ 27 እና በአፄ ናኦድ ትምህርት ቤቶች የመደበኛ ትምህርቱን እንደተከታተለ የህይወት ታሪኩ ያሳያል።
አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ በ1967 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ ስራ መጀመሩም ታውቋል።
ኦቴሎ፣ ኤዲፐስ ንጉሥ፣ ሐምሌት፣ ቴዎድሮስ፣ ንጉሥ አርማህ፣ መቃብር ቆፋሪውና የሬሣ ሳጥን ሻጩ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለ ካባ ባለ ዳባ፣ መልዕክተ ወዛደር እና ሌሎችም ታዋቂነትን ያተረፉለት ተውኔቶችን በብቃት ተውኗል።
ፍቃዱ ባለፉት ወራት በኩላሊት ህመም ሳቢያ ሲቸገር ቆይቷል፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህም አድናቂዎቹ፣ የሙያ ባልደረቦቹና ሌሎችም ውጭ ሀገር አቅንቶ እንዲታከም ብር አሰባስበው ነበር።
አርቲስት ፍቃዱ ከወዳጆቹና ከአድናቂዎቹ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 200 ሺህ ብር ያህሉን ለአንዲት ኩላሊት ታማሚ በመለገስ ወደ ፀበል ማምራቱንም የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

No comments:

Post a Comment