Monday, August 27, 2018

አቶ አብዲ ኢሌ በተለያዩ ወንጀሎች ይጠየቃሉ ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 21/2010) የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አብዲ መሀመድ ዑመር አብዲ ዒሌ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች እንደሚጠየቁ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

አቶ አብዲ ዒሌ ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፖሊስ አስታውቋል።


እሳቸውና ሌሎች ሰባት የሶማሌ ክልል የቀድሞ አመራሮችና ግለሰቦችም ያለመከሰስ መብታቸው መነሳቱም ተገልጿል።

አቶ አብዲ ዒሌ በተያዙበት ወቅት በመኖሪያ ቤታቸው በርካታ የጦር መሳሪያዎች ከመሰል ጥይቶች ጋር መገኘታቸውንም ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል። ብዙዎች ተገድለዋል። ሺዎች ሀገር ጥለው ተሰደዋል።

በርካቶች በእስር ቤት ፍዳ መከራቸውን በልተዋል። በእሳቸው ዘመን ክልሉ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፡ ስር በሰደደ ሙስና፡ በፍትህ መጓደል፡ በዘረፈ ብዙ ማህበራዊ፡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ በደሎች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብቷል።

የሶማሌ ክልል ተወላጆች በዓለም ዙሪያ የጮሁለት፡ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በተደጋጋሚ ስጋታቸውን ያነሱበት የአቶ አብዲ ዒሌ አምባገነናዊ የጭቆና አስተዳደር በመጨረሻም ፍትህ እጅ ወድቋል።

በቅርቡ በጂጂጋና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች ለተፈጠረውና ለአስቃቂ የሰው ልጅ ህይወት መጥፋት፡ ለንብረት ውድመትና ለአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል በዋናነት እጃቸው እንደሚገኝበት የሚነገርላቸው የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ባለፉት 10 ዓመታት በክልሉና አጎራባች አከባቢዎች በተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች የሚጠየቁ እንደሚሆን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

ለሶስት ሳምንታት በቁም እስር እንደነበሩና ጥበቃ ሲደረግላቸው እንደቆዩ የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ በጊዜያዊነት ከሚኖሩበት መኖሪያ ቤት ተይዘው ወደ እስር ቤት መግባታቸው ተገልጿል።

የእሳቸውና የሌሎች ሰባት የቀድሞ የክልሉ አመራሮች ያለመከሰስ መብት ከተነሳ በኋላ በዛሬው ዕለት የእስር እርምጃው መውሰዱን ነው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ የተቻለው።

አብዲ ዒሌ በተያዙበት ወቅት በመኖሪያ ቤታቸው 5 ክላሽ የጦር መሳሪያ 4 ሽጉጦችና መሰል ጥይቶች መገኘታቸውም ተገልጿል። አብዲ ዒሌ ከጂጂጋው ቀውስ በፊት በሰጡት መግለጫ በክልሉ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ያቀዱትና በጉልበት እንድንፈጽመው ያደረጉት የህወሀት መሪዎች በተለይም አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

አሁን በአቶ አብዲ ዒሌ ላይ የተወሰደው እርምጃ በሶማሌ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዘረፋ ተግባር እጃቸው የሚገኙበትን የህወሀት ጄነራሎችና አመራሮች ላይ የሚቀጥል ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

የፖለቲካ ተንታኞች አብዲ ዒሌ አስሮ ሌሎችን የሚተው ፍትህ ጎዶሎ መሆኑን በመጥቀስ የሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋትን መነሻ ያደረገ እርምጃ ወደፊት ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል።

አቶ አብዲ ዒሌ መታሰራቸው እንጂ በአሁኑ ጊዜ በየትኛው እስር ቤት እንደሚገኙ የተገለጸ ነገር የለም። ኢሳት ያነጋገራቸው አንዳንድ የሶማሌ ክልል የመብት ተሟጋቾች የዛሬው የመንግስት ውሳኔ በክልሉ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማስፈን ትልቅ ትርጉም የሚኖረው ነው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል አዲሱ ፕሬዛዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር ባለፈው ቅዳሜ በይፋ ስራቸውን መጀመራቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment