Wednesday, August 29, 2018

የአቶ በረከት የዝወራ ዘመን አክትሟል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ--ነሐሴ 23/2010)በአቶ በረከት ይዘወር የነበረው የብአዴን የአመራር ዘመን ማክተሙን የአማራ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ገለጹ።

ሃላፊው ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ አቶ በረከት የድርጅቱ መስራች በመሆናቸው እናከብራቸዋለን ነገር ግን እሳቸው በሞግዚትነት የሚያሽከረክሩት ድርጅት እንዲሆን ግን አንፈቅድም ብለዋል።

አቶ በረከት በስብሰባው ላይ እንዳልገኝ የተደረኩት አመራሮቹን ስለምሞግታቸው ነው ያሉትም ፍጹም የማይመስልና ያኛው ዘመን አክትሞ የሰዎች ሃሳብ በነጻነት የሚስተናገድበት መድረክ መፈጠሩን ሊረዱ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ይልቅ አቶ በረከት ጊዜው ያለፈበትን ታሪክ ከሚያወሩ በአደባባይ ወተው የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ቢጠይቁ ይሻላል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/በነሐሴ 17ና 18 ባደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው የድርጅቱን ሁለት ነባር አምራሮች እስከ መስከረም አጋማሽ ድረስ ማገዱ ይታወሳል።አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን
ይህን ተከትሎም አቶ በረከት ስምኦን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ የተላለፈባቸው ውሳኔም ሆነ ድርጅቱ እየሄደበት ያለው ርቀት አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ውሳኔውም ቢሆን እሳቸው በሌሉበት የተላለፈና እራሳቸው የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በስበሰባው ላይ እንዲገኙ ቢጠይቁም እንዳለተፈቀደላቸው ነው የተናገሩት።
አሁን ያሉት የድርጅቱ አመራሮች ይህን ያደረጉት ደግሞ ከእሳቸው የሚነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ አቅም ስለሌላቸው ነው ብለዋል።
የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አቶ በረከትን ወደ ባህርዳር መተው በጉባኤው ላይ እንዳይሳተፉ የሚያደርጋቸው አንዳችም ስጋት የለም።
እሳቸውም ቢሆን የዋስትና መብቴ እንዲከበር  አቅርቤያለሁ ያሉት ጥያቄ ለማንና መቼ እንዳቀረቡ የሚታወቅ ነገር የለም ብለዋል አቶ ንጉሱ።
አቶ ንጉሱ እንደሚሉት አቶ በረከት የድርጅቱ መስራች በመሆናቸው እናከብራቸዋለን ነገር ግን በእሳቸው ይዘወር የነበረው ድርጅት ሕልውና ግን ማክተሙን ሊረዱ ይገባል ብለዋል።--ዛሬ ያለው አመራር የክልሉን መብትና የሕዝቡን ወቅታዊ ጥያቄ ለመመለስ እየተጋ ያለ አካል ነው ብለዋል።
በስብሰባው የሚነሱት ሃሳቦች ስለ አማራ ሕዝብ መብት መከበርና ከወጣቶች ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥበት መድረክ ሆኖ ሳለ አቶ በረከት የአሁኑ አመራር እኔ የማነሳቸውን ጥያቄዎች ይፈራል ማለታቸው ትዝብት ላይ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል ብለዋል አቶ ንጉሱ።
በተለይ ባለፉት ሶስት አመታት የአማራ ህዝብን ነጻነትና ትግል ሕዝቡ እንዳይወያይበት በማድረግና አጀንዳውን በመጠምዘዝ፣አመለካከቱም ቢሆን የትምክህተኛና የነፍጠኛ ነው በማለት ሲያሸማቅቁ መቆይታቸውንም አቶ ንጉሱ ከመግለጽ ወደ ኋላ አላሉም።
አቶ በረከት በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ በሕዝቡ ብሎም በአመራሩ ውስጥ ያለውን ችግር እየተነተኑ ሲሞግቱ ፣የነበሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ሲነግሩን ተቀብለናል።የማንቀበለውንም እንደማንቀበለው ተናግረናል።
የእሳቸው ሁሉን አግበስብሳችሁ ውሰዱ እኔ ምለው ትክክል ነው የሚለውን የአምባገነንነት አካሄድ እንደማንቀበለው በአደባባይ ስንናገር ግን ለአቶ በረከት ሊዋጥላቸው አልቻለም ብለዋል።
ምክር ቤቱ የወሰደው ርምጃ በኤርትራ መንግስት ትዕዛዝ ነው ያሉትም በፍጹም የተሳሳተና እርስ በርሱ የሚጋጭ ይሆናልና እራሳቸውን ቢያዩ ጥሩ ነው ብለዋል አቶ ንጉሱ።
አቶ በረከት ሊያውቁት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ከዚህ በኋላ ብአዴን በማንም የማይዘወርና ሞግዚት የማያስፈልገው ተቋም መሆኑን ነው።
ይልቅ አቶ በረከት እየሄዱ ያሉበትን መንገድ ትተው የበደሉትን ሕዝብ ይቅርታ ቢጠይቁና እየተካሄደ ካለው ሰላማዊ ትግል ጋር ቢቀላቀሉ ይሻላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment