Thursday, August 2, 2018

በደቡብ ክልል በተፈጠረ ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 26/2010) በደቡብ ክልል የም ወረዳ በተፈጠረ ግጭት በሰዎች ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።
በወረዳው ዋና ከተማ ሳጃ ግጭቱ የተከሰተው የመልካም አስተዳደር ችግር በመነሳቱ ነው ተብሏል። በእምነት ሰበብም በርካታ ሰዎች ሲገደሉ ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ የሚወስደው መንገድ በግጭት ምክንያት ተዘግቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በደቡብ ክልል የም ወረዳ ሳጃ ከተማ ከሐምሌ 4 ጀምሮ ሰላም ርቋት መሰንበቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በተለይ ደግሞ ሰሞኑን ግጭቱ ተባብሶ በርካታ ሰዎች ሲገደሉ ንብረትም ወድሟል።–ቤቶች ተቃጥለዋል።

ከፍተኛ ጉዳትም በሰዎች ላይ ደርሷል።በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣የግጭቱ መንስኤ የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረው ነው ተብሏል።
ሃይማኖትን መነሻ ያደረገ ግጭት እንደነበርም በዘገባው ተመልክቷል። ጥያቄዎቻችን ይመለሱልን በሚል በተፈጠረው ግጭት በርካታ ዜጎች ጉዳት ደርሶብናል ይላሉ።
ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ ሰዎች እንዲያዙና ለሕግ እንዲቀርቡ የአካባቢው ሰዎች ጠይቀዋል። የሳጃ ከተማ በአሁኑ ወቅት መረጋጋቷ ይነገራል።
በሌላ ዜና ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ የሚወስደው መንገድ ለ4 ሰአታት ያህል ተዘግቶ መቆየታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
የግጭቱ መንስኤ አንድ በምህረት የተለቀቀን ግለሰብ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ለማፈን በመሞከራቸው ነው ተብሏል።
ለመታፈን ሙከራ የተደረገበት ግለሰብ አራት አመት ከታሰረ በኋላ በይቅርታ ቦርድና በፕሬዝዳንት ሙላቱ ይቅርታ ተደርጎለት የተለቀቀ መሆኑም ታውቋል።
ግለሰቡን ለማፈን የሞከሩት የሕወሃት ሰዎች መሆናቸውን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።
ፖሊስ አካባቢውን የዘጉትን ሰዎች በማስለቀቅ ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ የሚወስደውን መንገድ ለትራፊክ ክፍት ማድረጉ ተነግሯል።

No comments:

Post a Comment