Monday, August 27, 2018

ብአዴን ወሳኝ የሚባሉ ርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 21/2010) የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ብአዴን/ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ የሚባሉ ርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ።

በዚሁም መሰረት የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ እንደሚሻሻልና የድርጅቱ ስያሜም እንደሚለወጥ ገልጿል። የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው ያልተለመደ መግለጫ ብአዴን የሚመራበትን ርዕዮት ሊቀይር እንደሚችል አስታውቋል።


ድርጅቱ የግለሰብ መብትና የቡድን መብት ተጣጥመው እንዲከበሩ ጠይቋል። የክልል አስተዳደራዊ ወሰኖች እንደገና እንዲሻሻሉ እንደሚታገልም ነው ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።

በዚሁም መሰረት ለሕዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ለሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በሕዝብ ነጻ ተሳትፎ እንዲፈቱም ብአዴን እታገላለሁ ብሏል። ይህ አገላለጽ የወልቃይት ማንነት ጥያቄን ይመለከታል።

ማሻሻያ ሳይደረግባቸው የዘለቁትን የሕገመንግስት ድንጋጌዎችንም የሕዝብ ጥያቄ እስከሆኑ ድረስ በበጎ እንመለከተዋለን ነው ያለው የብአዴን መግለጫ።

ሕዝባዊ ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ባልቻሉ የድርጅቱ አመራሮች ላይም ርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

ከድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን እስከ ድርጅቱ ጉባኤ ድረስ ማገዱን ማስታወቁ ይታወሳል። ይህን የማጥራት እንቅስቃሴም አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል ብአዴን።

የጥረት ኮርፖሬትና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋሞችም ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት እንዲሆን ወስኗል።አፈጻጸሙ በሕግ እንደሚወሰን በመግለጽ።

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ፣የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋም ያልተያዘበት ነበር ሲል የብአዴን መግለጫ አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment