Thursday, July 6, 2017

ዩኤንድፒ የአፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ተናኘወርቅ ጌቱ የጓደግኛቸውን ልጅ ካለውድድር ቀጠሩ

ኢሳት ዜና – ሰኔ 29, 2009
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የጠቅላይ ሚንስትሩ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አማካሪ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ሴት ልጅ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ( ዩኤንድፒ ) በአባቷ እገዛ ያለውድድር እንድትቀጠር መደረጉን አንድ አለም አቀፍ የፕሬስ ተቋም አጋለጠ ። ኢንተር ሲቲ ፕሬስ የተሰኘውና በተባበሩት መንግስታት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራው የሚድያ ተቋም እንዳለው የአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ጓደኛ የሆኑትና የዩኤንዲፒ የአፍሪካ ዳይሬክተር አቶ ተናኘወርቅ ጌቱ ሳሌም ብርሃኔ የተባለችን ሴት ልጅ ያለምንም ውድድር እና ህጋዊ አሰራር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንድትቀጠር ትእዛዝ ሰጥተዋል ። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2013 በዩኤንዲፒ ያለምንም ውድድር እንድትቀጠር የተደረገችው የአምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ ልጅ እንደገና የመዋቅር ለውጥ በተደረገበት በ2016 ጊዜም ከፍተኛ የደረጃ እድገት እንድታገኝ መደረጉን ኢንተር ሲቲ ፕሬስ አጋልጧል ። እንደገናም በ2017 ምንም አይነት የስራ ውድድር ማስታወቂያ ሳይወጣ ወደ ቋሚ የኮንትራት ውል ተሸጋግራ በደረጃ ላይ ደረጃ ፤ በእድገት ላይ እድገት እንደተጨመረላት በዘገባው ተገልጿል ። ሳሌም ብርሃኔ በዚህ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆኗን በሚመለከት ኢንተር ፕሬስ ሲቲ ለዩኤንዲፒ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱን
ጨምሮ አስታውቋል ። በዩኤንዲፒ የአፍሪካ ዳይሬክተር የጓደኛቸውን የአምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስን ልጅ በዝምድና ከማስቀጠር አልፈው በሚሰሩበት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአንድ መጠነኛ የጉዞ ስራ እስከ 11 ሺህ ዶላር የማወራረጃ ሂሳብ እንዳቀረቡም ኢንተር ሲቲ ፕሬስ አጋልጧል ። የሂሳብ ማወራረጃ ሰነዱንም የሚድያ ተቋሙ ይፋ አድርጓል ። ይህንን የሙስና ቅሌት ያጋለጡትና መረጃውን የሰጡት በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ ) የሚሰሩ ሰራተኞች መሆናቸውንም የሚድያ ተቋሙ ጠቁሟል። መረጃውን የሰጡት ሰራተኞች ለደህንነታቸው እንደሚፈሩና ጉዳዩን በሚስጥር መስጠታቸውንም ለማወቅ ተችሏል ። የተባበሩት መንግስታት አሰራር ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን በርካታ የማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ አድርጊያለሁ ቢልም እውነታው ግን አሁንም ከሙስና ያልጸዳ መሆኑን የአምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ ልጅ የስራ ቅጥርና የእድገት ሁኔታ ትልቅ ማሳያ ነው ተብሏል። የሙስና ቅሌቱ ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እና ለዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጎቴሬዝ በሚስጥር እንዲደረስ መደረጉንም ዘገባው አመልክቷል ። እናም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ያለው የቅጥርና የባለሙያ የመመልመል አሰራር በዘመድ አዝማድ ፥ በዘርና በሙስና የተተበተበ መሆኑን የአምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ልጅ ሳሌም ብርሃነ ጉዳይ እንደምሳሌ ሆኖ ቀርቧል ። አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ከዚህ ቀደም ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ስልጣናቸው ጋር በተያያዘ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በባንካቸው ውስጥ ስለነበር ከባለቤታቸው ጋር ሲለያዩ የንብረት ጥያቄ ተነስቶባቸው ግማሹን ገንዘብ በፍርድ ቤት ትዛዝ እንደሰጡ በሳቸው ዙሪያ የተጻፈ መረጃ ያመልክታል ።

No comments:

Post a Comment