Thursday, July 13, 2017

የአዲስ አበባ የግብር መክፈያ ቦታዎችም በአቤቱታ አቅራቢዎች እየተጨናነቁ ነው 

ሐምሌ ፮ ( ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባ የግብር መክፈያ ቦታዎችም በአቤቱታ አቅራቢዎች እየተጨናነቁ ነው የእለታዊ ገቢ ግብር አሰራርን በመቃወም በአምቦ ከተማ ዛሬ ተቃውሞ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ አንድ የፌደራል ፖሊስ መኪና ሲቃጠል ፣ አንድ አውቶቡስና ሌሎች የመስሪያ ቤት መኪኖችም ተሰባብረዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ 11 ሰአት ድረስ በከተማዋ ተኩስ ይሰማ ነበር። ወደ ወለጋ የሚወስደው መንገድም በድንጋይ ተዘጋግቷል። በከተማዋ ያሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የንግድ ቤቶችም ተዘግተዋል። በአዲስ አበባ ደግሞ የግብር መክፈያ ቤቶች በአቤቱታ አቅራቢዎች ተጨናንቀው ታይተዋል። በየወረዳው የሚገኙ ጽ/ቤቶች በአቤቱታ አቅራቢዎች በመጨናነቃቸው ፣ ባለስልጣናቱ “የምትችሉትን ክፈሉና ሌላውን ቀስ ብላችሁ ትከፍላላችሁ” በማለት ለማረጋጋት ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል። ነጋዴዎች ግን በባለስልጣኖች በኩል የሚሰጠውን መልስ የሚቀበሉት አልሆነም። በዲላ ነጋዴዎች ግብር አንከፍልም በማለት በአንድ ድምጽ እየተናገሩ ሲሆን፣ ድምጻቸውን ለማሰማት የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት የሚያደርጉትን ሙከራ ከንቲባው ለማጨናገፍ እየተሯሯጠ መሆኑን ወኪላችን ገልጿል።


No comments:

Post a Comment