Tuesday, July 4, 2017

ለቤት ግንባታ በአለም አቀፍ ጨረታ የተመዘገቡ የውጭ አገር ኩባንያዎች ወደ ስራ አለመግባታቸው ተገለጸ

ኢሳት ሰኔ 27/2009
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለቤት ግንባታ ባወጣው አለም አቀፍ ጨረታ 28 የሚጠጉ ደረጃ አንድ የውጭ ኮንትራክተሮች ተወዳድረው የተመረጡ ቢሆንም አንዳቸውም ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ከዛሬ ሁለት አመት በፊት የኮንስትራክሽን ሚኒስትሩና የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑት አቶ ድሪባ ኩማ በሰጡት የጋራ መግለጫ የውጭ ኮንትራክተሮችን በመኖሪያ ግንባታ ዘርፍ ለማሳተፍ ቅድመ-ዝግጅቱ የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው በጥቂት ቀናት ወደ ስራ ይገባሉ ቢሉም ባልተገለጸ ምክንያት መግለጫው ተፈጻሚ መሆን እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል።
በአለም አቀፍ ጨረታ የተመዘገቡት የውጭ ሀገር ኩባንያዎች እንዲቀሩ የተደረገው በገንዘብ እጥረት መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች የህዉሓት መራሹ መንግስት ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ በበጀት ያልተደገፈን እቅድ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የከተማና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶ/ር አምባቸው መኮንን የ2009 በጀት አመት የእቅድ አፈጻጸማቸውን ለኢህአዴግ ፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት በበጀት ያልተደገፉ እቅዶች መስሪያቤታቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተው በይፋ ገልጸዋል። ዶ/ር አምባቸው መኮንን እንደገለጹት ከሆነ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 750 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ቢሆንም፤ እቅዱ በበጀት ያልተደገፈ በመሆኑ ማስፈጸም እንደማይቻል በሪፖርታቸው አስታውቀዋል። ሚኒስትሩ አያይዘው እንደገለጹት ከሆነ ፕሮጀክቶቹ በገጠማቸው የፋይናንስ አለመኖር ምክንያት በርካታ የስራ ተቋራጮችና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ስራ በማቆም የመበተን እጣ ፈንታ ደርሷቸዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና በመንግስት በጀት ፋይናንስ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ሌሎች አማራጮች መታየት እንዳለባቸው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ለኢህአዴግ ፓርላማ ይፋ ማድረጋቸውን ኢሳት መዘገቡ የሚታወስ ነው።

No comments:

Post a Comment