Monday, July 17, 2017

ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ከግብጽ ጋር ለመተባበርና ለመደራደር ምንጊዜም ዝግጁ መሆኗን ገለጸች ።

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 10/2009) ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ከግብጽ ጋር ለመተባበርና ለመደራደር ምንጊዜም ዝግጁ መሆኗን ገለጸች ። የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ ውሀ ለመሙላት መዘጋጀቷን ተከትሎ ጉዳዩ እያሰሰበው መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል ። ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር የተመራ ቡድን አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳን በጉዳይ ላይ ማነጋገሩ ታውቋል። የግብጽ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት የኢትዮጵያ መንግስት በኣባይ ግድብ ጉዳይ ላይም ሆነ በሁለቱ ሀገራት የትብብር ግንኙነቶች ዙሪያ ለመተባበርና ለመደራደብ ዝግጁ ነው። አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ለግብጽ የልዑካን ቡድን እንዳረጋገጡትም ኢትዮጵያ የሌላውን ሀገር ጥቅም በሚጎዳ መልኩ የራሷን ጥቅምና እድገት አትመኝም ። አቶ ኣባ ዱላ ይህንን ቢሉም ግን የግብጽ መገናኛ ብዙሀን ኢትዮጵያ በያዝነው ሀምሌ ላይ የአባይ ግድብን በውሀ መሙላት
ስትጀምር የወንዙ ውሃ በእጅጉ እንዲሚቀንስ የውሀ ባለሙያዎችን ጠቅሰው እየዘገቡ ይገኛሉ። በአፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳና በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር የተመራው የልዑካን ቡድንን ለመገናኘትና ለመወያየት ያበቃቸውም ይሄው ጉዳይ መሆኑን ዴይሊ ኒውስ የተባለ የግብጽ ጋዜጣ ዘግቧል ። አል ሸሩክስ የተባለው የግብጽ ጋዜጣ እንዳለው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በአባይ ግድብ ተጽዕኖ ላይ የሚያደርጉትን ጥናት ሳያጠናቅቁ ውሀ የመሞላቱ ስራ በመጀመሩ ወንዙ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል ። የግብጽ የውሀ ባለስልጣናት ግን ሞላ የተባለው ውሀ ጎርፍ ያስከተለው እንጂ ሌላ አይደለም እያሉ ነው ። ይህም ሆኖ ግን በአባይ ግድብ ምክንያት ወይም ውሀው መሙላት ሲጀምር የግብጽ ውሀ መቀነሱ እንደማይቀር ስጋት እንዳላቸው የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሜህ ሽኩር ለኢትዮጵያዊው አቻቸው ለዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አረጋግጠውላቸዋል ተብሏል። ያም ተባለ ይህ ግን መተማመን እንደሌላቸውና ጉዳዩ አሁንም በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት ማስከተሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

No comments:

Post a Comment