Thursday, July 13, 2017

በአለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ የአለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጣና ሃይቅ በእምቦጭ አረም መስፋፋት ምክንያት የመጥፋት አደጋ ተደቅኖበታል።

ኢሳት-ሐምሌ 6/)2009 በአለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ የአለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጣና ሃይቅ በእምቦጭ አረም መስፋፋት ምክንያት የመጥፋት አደጋ ተደቅኖበታል።ከዚህ ባልተናነሰ ግን በባህር ዳር ከተማና በሃይቁ ዙሪያ የሚገኙ የአገልግሎትና መንግስታዊ ተቋማት ወደ ሃይቁ የሚለቁት ፍሳሽ ችግሩን እንዳባባሰው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ከአማራ ክልል ምክር ቤት ህንጻ ፣ ከመስተዳድሩ የዘርፉ ቢሮዎች ፣ከ3 ሺ በላይ ታሳሪዎችን ከሚይዘው ወህኒ ቤት ፣ ፖሊ ቴክኒክን ጨምሮ ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚወጡት ፍሳሾች የሃይቁን ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዱት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ከእነዚህ መንግስታዊ ተቋማት በተጨማሪ በባህር ዳር ዙሪያ የሚገኙት የሼሕ መሃመድ አላሙዲን ንብረት የሆኑት የጣናና አቫንት ሪዞርት ሆቴል፣የወይዘሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ ንብረት የሆነው ግራንድ ሆቴል፣የአቶ ጠብቀው ባሌ ንብረት የሆነው ፓፒረስ ሆቴል ፣ሆም ላንድ ሆቴልና ከአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚወጣው የመጸዳጃ ቤት እንዲሁም ሌሎች የቆሻሻ ፍሳሾች ሃይቁን ለብክለት እየዳረጉት መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል። የክልሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት ለክልሉ ምክር ቤት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረበው ሪፖርትም በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች የመጸዳጃ ቤት ቆሻሻን ከፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ጋር በማገናኘት የጣና ሃይቅንና የአባይ ወንዝን እየበከሉ መሆኑን ይገልጻል። ባለቤቶቹ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ተጫማሪ እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ያመለክታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመንግስታዊና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚወጣው ፍሳሽ የሚይዛቸው እንደ ፎስፌትና ናይትሬት የመሳሰሉ ኬሚካሎች በጣና ሃይቅ ላይ አደጋ ለጋረጠው የእምቦጭ አረም መስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ባለሙያዎች ይናገራሉ። የእምቦጭ አረም ከቆሻሻው የሚወጣውን ፎስፌትና ናይትሬን እየተመገበ እንደሚስፋፋ በመግልጽ በስፋቱ 350 ሺ ሄክታር ከሚሆነው አጠቃላይ የጣና ሃይቅ ገጽታ 50 ሺ ሄክታር ያህሉን በእምቦጭ አረም እንደተወረረ ባለሙያዎች አረጋግጠዋል። በዚሁም ሳቢያ የጣና ሃይቅ ሕልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ብዙዎቹን እያሳስበ ይገኛል ።


No comments:

Post a Comment