Thursday, June 18, 2015

የሟች ሳሙኤል አወቀ ጉዳይ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች እየተዘገበ ነው።

ኢሳት ዜና (ሰኔ 11, 2007)

ሰኞ ምሽት በደብረማርቆስ ከተማ የተገደለው እጩ የፓርላማ አባልና የህግ ባለሙያ ሳሙኤል አወቀን በተመለከተ አለም አቀፍ ሚዲያዎች የዜና ሽፋን እየሰጡት ይገኛሉ። የ ሀያ ሰባት አመቱ ወጣት ሳሙኤል አወቀ ማንነታቸው ባልታወቁ ሁለት ሰዎች አሰቃቂ ድብደባ ከተፈጸመበት በኋላ ህይወቱ ማለፉን ብሉምበርግ የዜና ወኪል ዘግቧል።



የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ጸሀፊ የነበረው የፓርላማው እጩ ተወዳዳሪ ሳሙኤል አወቀ ባለፈው ወር ከተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ጋር በተገናኘ የሞት እርምጃ ሊወስድበት እንደሚችል የሚገልጽ ዛቻ ሲፈጽምበት መቆየቱን የዜና ወኪሉ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል ።

ይሁንና የመንግስት ኮሙኒከሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስቴር አቶ ሬድዋን ሁሴን አንድ ተጠርጣሪ መያዙን፣ ድርጊቱን ከህግ አለመግባባት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

የህግ ባለሙያ የነበረው ሟች ወጣት ሳሙኤል በግንቦት ወር በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ከፍተኛ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ብሉምበርግ አውስቷል ።

አቶ ሬድዋን ሁሴን የግድያው መንሰኤ ከሟች ስራ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል ቢሉም የእጩ ተወዳዳሪው የቅርብ ጓደኞች ወጣት ሳሙኤል ከሚደርስበት የግድያ ዛቻ በስተቀር የግል ጠብ እንዳልነበረው አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ በወጣት ሳሙኤል ላይ የተፈጸመው ግድያን እንደሚያወግዝና ወንጀለኞቹ የመንግስት አካላት እንደሆኑ እረቡ ባወጣው የሀዘን መግለጫ ገልጿል።
በገዢው የኢህአዴግ መንግስት በየጊዜው የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ድርጊቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ያስታወቀው ፓርቲው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የግፍ ሰርአት ያለውን አገዛዝ ለመታገል የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል ።
ሟች ሳሙኤል በህይወት እያለ በደህንነት ሀይሎች ሲደርስበት የነበረውን የግድያ ዛቻ ያወሳው ፓርቲው ወጣቱ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነና ጥበቃ እንዲደረግለት ጥያቄን ቢያቀርብም በተገላቢጦሽ ዛቻና ማስፈራሪያና ሲደርስበት መቆየቱን አመልክቷል ።
"ብታሰርም ፤ ብገደልም ይህን ሁሉ የማደርገው ለሀገሬና ለነጻነቴ ነው" ሲል የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ የነበረው ወጣት ከመሞቱ በፊት ማስታወሻን ጽፎ እንደነበረ ያወሳው ሰማያዊ ፓርቲ የሟች ቃል ከመቃብር በላይ ሆኖ እንደሚቆይ ገልጿል ።
ሜይል ኤንድ ጋርዲያን የተሰኘ ጋዜጣም የሟች ሳሙኤል ድርጊት በተመለከተ ረቡእ እለት ዘገባ ይዞ የወጣ ሲሆን የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ባለፈው ወር በኢትዮጵያ የተካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ከሟች ታሪክ ጋር በማዛመድ ዘገባዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ታውቋል።


No comments:

Post a Comment