Monday, June 1, 2015

ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር አብራችሁዋል በሚል የተያዙት ክስ ተመሰረተባቸው

ግንቦት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ጎንደር ዞን ማክሰኝት ከተማ ነዋሪ መሆናቸው የተነገረው አቶ ዘመነ ምህረቱ እና ሌሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረታባቸው ሪፖርተር ዘግቧል።አቶ ዘመነ የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት መሆናቸው በክሱ የተመለከተ መሆኑን የዘገበው ጋዜጣው፣ መስከረም 18፣ 2007 ዓም በጎንደር በሚገኘው የመኢአድ ጽ/ቤት ውስጥ አባላትን በመሰብሰብ ” የወያኔ መንግስት መውደቂያው ደርሷል።አንድ የቶር አውሮፕላን፣ 12 የጦር ጄኔራሎች ከድተው ወደ ኤርትራ ገብተዋል። ኢህአዴግ በጦር ካልሆነ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን አይለቅም። የህዝብ እምቢተኝነት በመፍጠር የወያኔን መንግስት መጣል አለብን፣ በ2007 ዓ.ም. የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ አይካሄድም፡፡ ወደ ምርጫው አንገባም፡፡ ሌላ አማራጭ መጠቀም አለብን…›› ” የሚል ክስ እንደተሰመረተባቸው ጋዜጣው ዘግቧል።በዚሁ መዝገብ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌትነት ደርሶ ተመሳሳይ ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ ወደ ኤርትራ ተሻግረው ከግንቦት7 ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ዶ/ር ክፈተው አሰፋ ጋር በመገናኘት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠና ወስደዋል ተብሎአል።በዚሁ መዝገብ ተከሰው የቀረቡት ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ መለሰ መንገሻ ሲሆኑ ፣ እርሳቸውም የአርበኞች ግንባር አባል ነበሩ ተብሎአል። ተከሳሹ ሰው በመመልመል ስራ ላይ መሳተፉንና በመንግስት ባለስልጣናትላይ ጠቃት ለመፈጸም ሲያጠና ነበር የሚል ክስ እንደተመሰረተበት ጋዜጣው ዘግቧል።


No comments:

Post a Comment