Thursday, June 11, 2015

አቶ ዳዊት አስራዳ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ ከፍሎ ታሰረ

• እስካሁን 36 ሺህ ብር ከፍሏል

የቀድመው አንድነት አመራር አቶ ዳዊት አስራደ ትናንት ግንቦት 3/2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በ5000 ብር ዋስ እንዲፈታ ዋስትና የተፈቀደለት ቢሆንም ገንዘቡን ካስያዘ በኋላ ዋስትናው እንደተነሳ ተነግሮት በእስር ላይ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ በትናንትናው ችሎት ፖሊስ ተከሳሾቹ ምስክሮችን ያባብሉብኛል በሚል ምስክሮችና መረጃዎችን አሰባስቦ እስኪያቀርብ ጊዜ ድረስ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቆ የነበር ቢሆንም አቶ ዳዊት አስራደ፣ አቶ አለነ ማህፀንቱና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ የ5000 ብር ደሞዝ ያለው የሰው ዋስ ወይንም ገንዘብ አስይዘው ከእስር እንዲወጡ ፈቅዶ ነበር፡፡


ይሁንና የአቶ ዳዊት አስራደ ቤተሰቦች መፍቻ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ሲሄዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ፖሊስ አቶ ዳዊትን ለቄራ ፖሊስ ጣቢያ ማስረከቡን እንደገለጸላቸው ጠበቃው አቶ ገበየሁ ይርዳው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የቄራ ፖሊስ ጣቢያም ከአሁን ቀደም አቶ ዳዊት አስራደ በተመሳሳይ ክስ ተፈቅዶለት የነበረውን ዋስትና ማንሳቱን በመግለጽ እንዳሰረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በተፈቀደለት ዋስትና መሰረት 5000 ብር ያስያዘውን አቶ አለነ ማህፀንቱን ፖሊስ መጀመሪያ ወደ ማታ እፈታዋለሁ፣ እንዲሁም ከቆይታ በኋላ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሎ እስር ላይ ቢያቆየውም አሁንም ድረስ ይግባኝ ሳይጠይቅ በእስር ላይ እንደሚገኝ ጠበቃው ገልፀዋል፡፡

መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰረው አቶ ዳዊት አስራዳ በተመሳሳይ ክስ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ እያስያዘ እንደገና በእስር ላይ የቆየ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ 25 ሺህ፣ በቀጣይነትም 6 ሺህ፣ እንዲሁም በትናንትናው ዕለት 5 ሺህ ብር በአጠቃላይ 36 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ እንደገና ታስሯል፡፡ አቶ ዳዊት አስራደና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ ሚያዝያ 14 መንግስት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ሰበብ በአንድ ጉዳይ ሁለት ክስ ተመስርቶባቸው በሁለት ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ በቄራና ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያም በፈረቃ ሲታሰሩ ቆይተዋል፡፡


No comments:

Post a Comment