Wednesday, June 3, 2015

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2006 በጀት ዓመት ያለምንም ማስረጃ ገንዘብ ከሚያወጡ መንግስታዊ ተቋማት መካከል የደህንነት ተቋም ዋንኛው መሆኑን አጋለጠ፡፡

ግንቦት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዋና ኦዲተር የ2006 ዓ.ም የመንግስት መ/ቤቶች የሂሳብ ሪፖርት ትላንት ለፓርላማው ያቀረበ ሲሆን በዚህ ሪፖርቱ ያለምንም ማስረጃ ገንዘብ ያወጡ 19 መንግስታዊ ተቋማት የተገኙ ሲሆን እነዚህ ተቋማት በድምሩ ከ473 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አውጥተው ተገኝተዋል፡፡ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ላቅ ያለውን ድርሻ ማለትም 274 ሚሊየን ብር ያወጣው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በቀጣይም በምክትል ጠ/ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ የሚመራው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር 111 ሚሊየን ብር፣ መቱ ዩኒቨርሲቲ 16 ሚሊየን ብር፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 12 ሚሊየን ብር፣ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 10 ሚሊየን ብር ወጪ አውጥተው ተገኝተዋል፡፡ዋና ኦዲተር በዚህ ወጪ ላይ በሰጠው አስተያየት ማስረጃ ያልቀረበለት ሂሳብ በቂ ማስረጃ እንዲቀርብበት ያሳሰበ ሲሆን አለበለዚያ ገንዘቡ ወደመንግስት ካዝና እንዲመለስ አዟል፡፡ዋና ኦዲተር አያይዞም ተሰብሳቢ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ78 መ/ቤቶች ከ 2 ቢሊየን ብር በላይ በደንቡ መሰረት ሳይወራረድ መገኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በወቅቱ ሂሳብ ከማያወራርዱት ተቋማት መካከል መከላከያ ሚኒስቴር 144. 2 ሚሊየን ብር፣ ፌዴራል ፖሊስ 64. 4 ሚሊየን ብር ድርሻ ወስደዋል፡፡


No comments:

Post a Comment