Friday, November 14, 2014

ሁሉም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች ውጤታቸው የሚሞላላቸው በምርጫው ለኢህአዴግ በሚያዘጋጁት የድጋፍ ሃይል መጠን ነው ተባለ

ኢሳት ዜና :- ትምህርት ሚኒስቴር ” የከፍተኛ ትምህርት የኢህአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሰራዊት ግንባታ አደረጃጃት ማንዋል፣ ለምርጫ 2007 የተሻሻለ” በሚል ርእስ ያዘጋጀውና ለኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች የቀረበው ሰነድ እንደሚለው በአገሪቱ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዚዳንቶች ውጤታቸው የሚሞላላቸው በምርጫው ለኢህአዴግ በሚያዘጋጁት የተማሪዎች የድጋፍ ሃይል መጠን ነው።

ሰነዱ የትምህርት ልማት ሰራዊትን በዩኒቨርስቲዎች ለማስፋፋት የተደረገው ስራ ብዙም ውጤት እንዳላስገኘ ጠቅሶ፣ ለዚህም ዋናው ምክንያት በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በአደረጃጃቱ ላይ አመኔታ በመጣታቸው ነው ብሎአል። የትምህርት ልማት ሰራዊትን ማደራጀት የፖለቲካ እንጅ የቴክኒክ ጉዳይ ባለመሆኑ ፣ በትምህርት ልማት የሚታቀፉ መሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የትምህርት ሴክተሩን እቅድ መተግበር ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካ ስእብናቸው የተገነቡና ኢህአዴግን የሚቀበሉ ተማሪዎች አድርጎ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል ሲል ሰነዱ ያመለክታል።



ማንዋሉ የትምህርት ልማት ሰራዊቱ 3 ክንፎች እንዳሉት ይጠቅሳል። ለምርጫ 2007 ዓም የምርጫ አሸናፊነት የሚያዘጋጁ ሁለቱ ክንፎች ማለትም የመንግስትና የህዝብ ክንፎች የሚባሉት ብቻ እንዲዳሰሱ መደረጉን ሰነዱ አመልክቶ፣ የልማት ሰራዊቱ እንቅስቃሴ ከፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ተያይዞ ከጫፍ ጫፍ የሚንቀሳቀስ ሃይል እንደሚሆን ገልጿል።

ሰነዱ ” በተለይም በአሁኑ ሰአት ፈተና ላይ የጣለን የምርጫ ጉዳይ እንደምናሸንፍ ቃል የተያዘበት ቢሆንም፣ ፈተናዎች የሚፈጠሩት በህዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑ ሃይሎች ማለትም በመንግስት ክንፍ በሚባሉት መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች አይቀለበስም ብሎ ማሰብ ስለማይቻል፣ በዚህም ቀድሞ መዘጋጀት ያለበትና ለሁከት እና ለብጥብጥ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው የህዝብ ክንፍ የሚባለው የተማረው ሃይል ሊሆን ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል ብሎአል።

ተማሪዎች በኢህአዴግ ላይ ያላቸው አቋም የወረደ መሆኑን ሰነዱ ይገልጻል። በማንኛውም ታቃውሞ ላይ በመገኘት ሰልፍ በማድመቅና ተቃውሞውን ከግብ ለማድረስ ተማሪዎች ሁነኛ መሳሪያ ናቸው የሚለው ሰነዱ፣ በየትኛውም ሀገር እንደታየው አደባባይን የመያዝ ህዝብን አስተባብረው ለተቃውሞ የማሳደም እድላቸው የሰፋ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህም አልፎ የኢህአዴግን የምከታ እርምጃ በመቃወም ለጠላት ጎራ ተሰልፈው የመታጠቅ እድላቸው ከፍተኛ ነው ብለአል።

- See more at: http://satenaw.com/amharic/?p=2444#sthash.vpcsqwHA.dpuf

No comments:

Post a Comment