Friday, November 14, 2014

ህወሓት በ2007 ምርጫ ሊሸነፍ እንደሚችል አመነ (አብርሃ ደስታ ከትግራይ)

ዓረና ፓርቲ በትግራይ ክልል ወረዳዎች በመዘዋውር ባሰብሰበው መረጃ መሰረት በ2007 በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ገዥው ፓርቲ የህዝብን ድምፅ ካከበረ ህወሓት በመላው ትግራይ ሙሉ በሙሉ ይሸነፋል። አንድ የህወሓት የስራ አስፈፃሚ አባል (ለግዜው ስሙ ይቅር) በዓዲግራት ከተማ ለተሰበሰቡ ከምስራቃዊ ዞን የተውጣጡ የህወሓት ካድሬዎች “እናንተ በምትፈፅሙት በደል ምክንያት በ2007 ምርጫ እንሸነፋለን። ግን አንዳንድ የምናደርጋቸው ነገሮች ስለሚኖሩ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አትቁረጡ። ለራሳችሁ ዕጣ ፈንታ ስትሉ በደንብ ስሩ” ማለቱ ታውቋል። ካድሬዎቹም “በናንተ (የላይኞቹ አመራሮች) ችግር ነው የምንሸነፈው፤ ህዝብ የማይቀበለውን ነገር እንድናሳምን ታስገድዱናላቹ” የሚል መልስ በመስጠታቸው የእርስበርስ ንትርክ መከፈቱ ታውቋል። ከስብሰባው በኋላ ካድሬዎቹ የንትርኩ ነጥቦች ለዓረና አባላት አስረድተዋል።



በዓረና እንቅስቃሴ የሰጉ የህወሓት መሪዎች ህዝብን በገንዘብ መደለል ጀምረዋል። ባሁኑ ግዜ የትግራይ ህዝብ በህወሓቶች በሦስት ደረጃዎች ተከፍሎ ግሬድ ተሰጥቶታል። ግሬድ A, B ና C። ግሬድ “A” ታማኝ የህወሓት ካድሬ፣ ግሬድ “B” መሓል ሰፋሪ፣ ግሬድ “C” ተቃዋሚ (ዓረና)። በዚሁ መሰረት ህወሓትን ለማገልገል ፍቃደኛ የሆነ ሰው (ታማኝ ካድሬ A) ለስብሰባ ይጠራና የማዳበርያን ዕዳ ለመክፈል የሚያግዘው 3000 ብር የውሎ አበል ተብሎ ይሰጠዋል። 3000 ብር ከተቀበለ በኋላ ተቃዋሚዎችን ይታገላል፣ ህወሓት እንዲመረጥ ያግዛል፣ ታማኝ የህወሓት አገልጋይ ይሆናል። ለህወሓት ታማኝ ያልሆነ ለስብሰባ አይጠራም፤ ገንዘብም አይሰጠውም። በ3000 ብር የምርጫ ድምፅ መግዛት ይሉታል እንዲህ ነው። የምርጫ ድምፅ እየተገዛበት ያለ ገንዘብ የህወሓት ሳይሆን በግብር መልክ የተሰበሰበ የመንግስት ገንዘብ ነው። መንግስት ብር አነሰኝ እያለ ግብር እየጨመረ ነጋዴዎች ንግዳቸውን ይዘጋሉ። ህወሓቶች ደግሞ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለምርጫ ጅንጀና ይጠቀሙታል።

የትግራይ አርሶአደሮች እንደዚህ በፖለቲካ ታማኝነት በዉሎ አበል መልክ ገንዘብ እየተሰጣቸው የማዳበርያ ዕዳቸውን መክፈል ከቻሉ ጥሩ ነው። ባንዳንድ አከባቢዎች ግን የዉሎ አበሉ መጠን ይለያያል። ለምሳሌ በደቡባዊ ምስራቅ ዞን ለየት ያለ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ህወሓቶች በሁሉም ዞኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ ታማኝ የተባሉ (ለምርጫ ሊያገለግሉ የሚችሉ) 200 የሳምረ አርሶአደሮች መለመሉ። አርሶአደሮቹ ሲመለመሉ “ለስብሰባ ትሄዳላቹ፣ 3000 ብር አበል ይሰጣችኋል፤ ስለዚህ 3000 ብሩን ለማግኘት በመጪው ሰኔ ላይ ለምትወስዱት ማዳበርያ 1200 ብር አሁን ክፈሉ” ይሏቸዋል። አርሶአደሮቹም 3000 ብሩን ለማግኘት 1200 ብር እንደምንም ብለው ከፈሉ። ከሳምረ ለስብሰባ ተብሎ ወደ ሕዋነ ተወሰዱ፤ ፖለቲካ ተጀነጀኑ። በመጨረሻ እነሱ 3000 ብር እየጠበቁ 640 ብር ብቻ እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው። ከ640 ም 600 ው መቆጠብ አለባቹ በሚል ሰበብ በህወሓቶች እጅ ሲቀር 40 ብር ብቻ ለትራንስፖርት ተሰጣቸው። አርሶአደሮቹ አሁን ቅሬታቸው አካፍለውናል።

አዎ! የህዝብ ድምፅ ከተከበረ ዓረና ሙሉ በሙሉ ያሸንፋል። እናም ህወሓቶች በሰለማዊ መንገድ ስልጣን ያስረክባል። የህወሓት ካድሬዎችም መብታቸው ተጠብቆላቸው በሰላም በሀገራቸው ይኖራሉ። ከፈለጉ በመንግስት መስራቤት በሙያቸው ተቀጥረው ይሰራሉ፣ ወይም ህወሓት ተቃዋሚ ፓርቲ አድርገው ለሚቀጥለው ምርጫ ለመወዳደርና ለማሸነፍ ይሞክራሉ። በሰለማዊ መንገድ ስልጣን ለማስረከብ ካልፈለጉ ግን በሃይል እስኪወገዱ ድረስ በስልጣን ይቆያሉ። በሃይል ከተሸነፉ እንደ የደርጎቹ ከሀገር ተጠርገው ይባረራሉ፤ የደርግ ባለስልጣናት ዕጣ ፈንታ ይቀምሳሉ።

ስልጣን ለህዝብ እናስረክብ፤ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር ይኑር። ስልጣን ለህዝብ ካላስረከብን ግን ሌላ ታጣቂ ሃይል ይነጥቀዋል። ከዛ ስልጣን ባላንጣን መምችያ ዱላ ይሆናል። ዱላው ከህዝብ ጋር መሆን አለበት።


No comments:

Post a Comment