Monday, November 10, 2014

ኢሕአዴግ ለምርጫ አልተዘጋጀም!

ይድነቃቸው ከበደ

ኢሕአዴግ በጭራሽ እራሱን ነፃ ለሆነ የምርጫ ውድድር እያዘጋጀ አይደለም !የፖለቲካ ሊቃውንት እንደሚያስገነዝቡት እና ዓለም አቀፍ ነባሪዊ ሁኔታ የሚያመላክተው ለምርጫ መሰረታዊ ከሆኑት ውስጥ ፤በእኩል ደረጃ ባይወንም እንኳን በአንፃራዊነት የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ነፃነት እና እኩል ተሣትፎ ሊኖር ይገባል፣ፓርቲዎችን ሊያወዳደሩ የሚችል ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ምርጫ ቦርድ እና ጉዳዩን ሙያዊ ስነምግባር መሠረት በማድረግ ለህዝብ መረጃ የሚያደርስ ነፃ ሚዲያ ያስፈልጋል፡፡እነዚህ መሰል ዋንኛ መስፈርቶች ባልተሟሉበት በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በመጪው ግንቦት ወር ነፃ ምርጫ ማካሄድ የሚታሰብ አይደለም፡፡

እንደ መግቢያ፡- በመዝገበ ቃላት አተረጓጎም መሠረት “ዲሞክራሲ ማላት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ማለት ሲሆን የመጨረሻውም ሥልጣን በሕዝብ ቁጥጥር ስር ያለ፣በቀጥታ በራሳቸው ወይም እነርሱ በወከሉት ወገን ብቻ በሥራ የሚተረጐምና በነፃ ምርጫ ስርዓት የተመረኮዘ ነው” ይላል፡፡ በአብርሃም ሊንከን አባባል “ዲሞክራሲ ከሕዝብ የወጣ ፣በሕዝብ የተመረጠና ለሕዝብ የሚያገልግል መንግስት ነው፡፡”በማለት የሰጠው ትርጓሜ በአብዛኛው ተቀባይነት ያገኝ ሃሳብ ነው፡ሦስቱ መሠረታዊ የመንግስት ምሶሶዎች ተብለው የሚታወቁት ማለትም ሕግ አውጪ፣ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ በሁለት መንገድ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡እነኚኽም አካሄዶች ቀጥተኛ እና የተወካይ ዲሞክራሲ ተብለው ተለይተው ይታወቃሉ ፡


ቀጥተኛ ዲሞክራሲ ዜጎች የሚመርጧቸው ምንም ዓይነት ተወካይ አይኖራቸውም፡፡ይህ ማላት ግን አስተዳዳሪ ወይም መሪ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡በማናቸውም ጉዳዮች ውሳኔ የሚወስነው በቀጥተኛ የህዝብ ተሳትፎ ነው፡፡ለየትኛውም የህዝበ ውሳኔ ጉዳዮች ፣ዜጎች በጋራ ተሰባስበው በመመክር በአንድ ዓይነት ስምምነት፣ ውይም በድምፅ ብልጫ ውሳኔ የሚያስተላልፉበት ስርዓት ነው፡፡የዲሞክራሲ እናት በመባል የምትታውቀው አቴንስ ከ4 ሺህ እስከ 7ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ስብሰባ በማካሄድ ነበር ቀጥተኛ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ተግባራዊ ታደርግ የነበረችው፡፡ይሁን እንጂ ከሕብረተሰብ ብዛት እና ከውስብስብነቱ አኳያ ለቀጥተኛ ዲሞክራሲ ተግባራዊነት የሚሰጠው ጥቅም ውስን በመሆኑ ብዙም ሳይጓዝ እንዲቀር ተደርጓል፡፡በአሁን ወቅት በዓለማችን በአብዛኛው ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የዲሞክራሲ ዓይነት የተወካዮች ዲሞክራሲ ነው፡፡እንዲህ ዓይነቱ ዲሞክራሲ ዜጎች የፖለቲካ ውሳኔዎችን የሚወስንላቸው ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ነው፡፡ተመራጮችሁም በበኩላቸው የመረጣቸውን ሕዝብ ወክለው ውስብስብ መንግስታዊ ሥራዎችን እውቀታቸውን፣ጊዜያቸውን እና ጎልበታቸውን ሰውተው ግልጋሎት ይሰጣሉ፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ፡- ከቀጥተኛ ዲሞክራሲ ይልቅ የተወካዮች ዲሞክራሲ ውጤቱ አጥጋቢ ባይሆንም፣ ተግባራዊ ለማድረግ ሙከራዎች ከዚህ ቀደም ተደርጓአል፡፡በተለይ በቀዳማዊ ንጉሳችን ኃይለ ስላሴ የተወካዮች ዲሞክራሲ ወደ አገራችን በማስገባት የዲሞክራሲ በዓላችን እንዲዳብር የተደረገው ጥረት እና ውጤት በታሪክ በአውንታዊ ጎን ተፅፎ የሚኖር ነው፡፡ይሁን እንጂ የተወካዮቹ አመራረጥ እና የሥራ ሂደታቸው ሲለካ ውጤቱ ምን እንደነበር ለታሪክ አዋቂዎች ቢተዉ የተሻለ ይሆናል፡፡ከዚህ ባለፈ በደርግ የተካሄደው የብሔራዊ ሸንጎ እና የኢሕአዴግ የ4 ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ለዜጎች ከሰጠው ፋይዳ ይልቅ የአምባገነን ሥርዓት ለማስቀጠል የሰጠው ጥቅም የበዛ ነው፡፡

ከምርጫ 1997 ዓ.ም ወዲህ፣ ገዥው መንግሰት የምርጫን መቃረብ ተከትሎ መንገዶችን ይሰራል፣ የጋራ መኖራይ ቤት ገንብቶ በዱቢ እና በረጅም ወራት ክፍያ ለተጠቃሚዎች ያስተላልፋል፣ለመንግሰት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ያደርጋል፣በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመጠቀም የምረጡኝ ዘመቻ ይጀምራል፣አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስልጠናና ጥምቀትን ያካሂዳል፣ዘላቂነት የሌላቸው ጊዚያዊ የሥራ እድሎችን በመፍጠር የሥራ አጦችን ካርድ ይነጥቃል፤ይህ ሣይሆን ሲቀር ኢ-ፍህታዊ ጥቅማ-ጥቅምን በመስጠት ደጋፊን ያበዛል፡፡ በተጨማሪም መቼም የማይፈፀሙ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በየቦታው የመሠረት ድንጋይ በመጣል ዳንኪራ ያስጨፍራል፣ከዚህም በላይ የሆነበትን ደግሞ ቃል ይገባል ፡፡እነዚህና መሰል የሆኑ ሁሉ ነገሮችን ማከናወኑ ለምርጫ ካርድ እንጂ ለዘለቂታዊ ልማት አይደልም፡፡የምርጫ ወቅት ሲቃረብ መንግስት ደፋ ቀና ደፈ ቀና የሚለበት ሥራ ሁሉ ለይስሙላ እንጂ ዘለቄታዊ ጠቀሜታ እንደሌለው ላለፉት አራት ዙር በተደረጉ ምርጫዎች ለማረጋገጥ ይቻላል ፡፡ በይበልጥ ደግሞ የፊታችን ግንቦት ወር ይካሄዳል የሚባለው ምርጭ በገዥው መንግሰት ቀጥተኛ ተፅኖ ስር በወደቀው ምርጫ ቦርድ እና ፣በመንግስት በኩል መንገስት ስል ኢሕአዴግ ወይም ወያኔ ለማለት እንደተፈለገ ግንዛቤ ይወሰድልኝ፡፡ምክንያቱ ደግሞ ገዥው ፓርቲ እና መንግስት ባልተለያዩበት ሥርዓት ውስጥ በመሆናችን ነው፡፡ስለሀኖም በእነዚህ ሁለት ሃይሎች ተፎካካሪ ወይንም አማራጭ በሆኑ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ይህ-ቀረሽ የማይባል ጫና እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡ችግሩ ደግሞ ቀጥተኛ በሆነ መንግድ የሚፈፀም ስለመሆኑ ከዚህ በታች በመጠኑ ለማመላከት ይሞከራል፡፡

የገዥው መንገስት ቀጥተኛ ጫና በፓርቲዎች፡-
በዓለም አቀፍ የተባበሩት መግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጉባሄ ባፀደቀው መግለጫ ኢትዮጵያም በፈረመችው ስለ መሰብሰብ እና መደራጀት መብቶች በሚከተሉው መልኩ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ “ የዜጎች የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ተግባራዊ ሂደት ገደብ በማይጣልበት ሁኔታ መከበር ሲኖርበት ነገር ግን ገደብ ቢደረግ እንኳን ገደቡ የዓለም ዓቀፍ ህግና ሰብዓዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ እና የእነዚህን መብቶች ሁለንተናዊ ጥበቃ እዉን የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡በተለይም ዜጎች የፖለቲካ እና የአይማኖት ለማስከበር የሚያደርጓቸው ተቃውሞዎች መደገፍ አለባቸው፡፡”የሚል ነው ፡፡

ይህ እጅግ በጣም ጠንካራ የሆነ ዜጎች በፖለቲካ የመደራጀት መብታቸውን የሚያስከበር ዓለም አቀፍ ሕግ ነው፡፡አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገመንገስት ይህን ህግ በመቀበል አካቶ ይገኛል፡፡እርግጥ ነው ህገመንግስቱ በራሱ ማሻሻይን የሚፈልጉ በርካታ አንቀፆች አሉት፡፡በዚህ አጋጣሚ ሰማያዊ ፓርቲ ዜጎችን በጋራ አግባብቶ በዘላቂነት ሊያገለግል የሚችል እና ለሕገመንግሰት መሠረት ወይም ምሶሶ የሚሆን “የዜጎች ቃል-ኪዳን ሰነድ ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ”የተሰኘ ሠነድ በማዘጋጀት ለህዝብ ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡ለዚህም መልካም ጅማሮ ለሰማያዊ ፓርቲ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ወደጉዳያችን ስንመለስ በዓለም አቀፍ እዲሁም በኢትዮጵያ ሕግ የፖለቲካን ዓላማ ለማስፈፀም ሕግን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት የተፈቀደ ነው፡፡ይሁን እንጂ ይህን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ኖራቸው በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቃወሚ ፓርቲዎች፤ ሰብዓዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች ይከበሩ፣የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፣ህዛባዊ መንግሰት ይመስረት በማለታቸው እና ለተግባራዊነቱ በመንቀሳቀሳቸው ብቻ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ለሞት፣ለእስራት፣ለስደት እና ለእንግልት እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡

ይህም በመሆኑ አብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላቶቺ ታስረዋል፣የመንግሰት ታጣቂ ሃይሎች በግልፅ እና በስውር በፓርቲ አባላት ወከባና እንግልት እየፈፀሙ ይገኛሉ፣ጠንካራ የሚባሉ የተቃዋሚ ሃይሎች የቀን-ተቀን ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ቢሮ መከራየት እንዳይችሉ አከራዩች በቀበሌ ካድሬዎች ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስባቸዋል፣ከብዙ ልፋት እና እንግልት በኋላ በሚያገኙት ቢሮ የፓርቲ አባላቶች ወደ ቢሮ ሲገብ እና ሲወጡ እየጠበቁ የመንግሰት ደንነቶች ወከባ ከፍ ሲልም ትንኮስ እየፈፀሙ ይገኛሉ፣ ፓርቲዎች ዋንኛ የተቋቋሙለትን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ከደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን በነፃነት አደባባይ ወጥተው ቅስቀሳ እንዲሁም ተቃውሞ ማድረግ የሞት ሽረት ትግል ነው፡፡በተለይ ደግሞ አዲስ ተመዝጋቢ አባላት የአባልነታው የእጩ ቀናት መቁጠር ከመጀመራቸው በፊት በመንግሰት ታጣቂ እና በካድሬዎች የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ እና ዛቻ ልጉድ ነው፡፡ከምንም በላይ ደግሞ የአባላትን ወራዊ መዋጮ እና ድጋፍ የፓርቲዎች የፋይናስ አቅም አይነተኛ መንግድ ነው፡፡ሆኖም ግን ይህ ገንዘብ በራሱ በቂ አይደለም፡፡ይህም በመሆኑ የፓርቲ አባላት ሣይሆኑ ደግፍ መስጠት ለሚፈልግ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ በልብ ሙሉነት ገንዘባቸውን እንዳይለግሱ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡የጉዳዩ አሳሳቢነት ምን ያኸል እነደሆነ ለማሳያ አነድ ምሣሌ መጥቀስ ይቻልል፤አቶ የሺዋስ አሰፋ፣አቶ አብታሙ አያሌው፣አቶ ደንኤል ሽበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ በማእከላዊ እስር ቤት በዋንኛነት የሚደረግባቸው ምርመራ “የፓርቲያችሁ የገንዘብ ምንጭ ምንድነው ? ማነው በቋሚነት ድጋፍ የሚያደርግላችሁ ?ገንዘቡ የት ነው የሚቀመጠው” የሚሉት ዘወትር የተለያየ የምርመራ ዘዴዎች በመጠቀም የሚጠየቁት ጥያቄ ነው፡፡ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ከላይ የተገለፁት የፓርቲ አባለት የተያዙት “በሽብር ወንጀል በመጠርጠር ነው”በማለት ገዥው መንግስት ገልፆአል ሆኖም በምርመራ ወቅት ግን የሚጠየቁት የፓርቲ ገንዘብ ወጪና ገቢ ነው፡፡ በአጠቃላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆን ብቻ ነጋዴው ከንግዱ፣ተማሪው ከት/ት፣ሰራተኛው ከስራው፣ገበሬው ከእርሻው፣አርብቶ አደሩ ከከብቶችሁ እየተፈናቀለ ይገኛል፡፡

ስለዚህም ተፈካካሪን የተቃወሚ ፓርቲን በእንዲህ መልኩ እያዳከመ እና አንዳንዶችን በጭራሽ ከወደቁበት እንዳይነሱ እያደረገ ይገኛል፡፡በእንዲህ መልኩ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ኢሕአዴግ ተፎካካሪ በመሆን ለመርጫ እራሱን እያዘጋጀ ነው እንዴት ሊባል ይቻላል ?

የገዥው መንገስት ቀጥተኛ ጫና በምርጫ ቦርድ ፡-
በየደረጃው ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 102 ላይ ይገኛል፡፡ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች ሹመታቸው ከመንግስት መልካም ፍቃድ የመነጨ ሲሆን አሰራራቸውም ለገዥው መንግስ በእጅጉ በጣም ያደላ ነው፡፡ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ህገመንግስቱን መሠረት አድርጎ ነጻ እና ገለልተኛ ነው ለማለት ከበድ ድፍረትን የሚጠይቅ ነው፡፡የስከዛሬውም የምርጫ ቦርድ የሥራ አንቅስቃሴ ለገዥው መንግስት ያለው ታማኝነት እና አገልጋይነት በድብቅ ሣይሆን በአደባባይ “እዩልኝ፣ስሙልኝ” እያለ በራሱ ላይ መስክሮ የእኛን መስክርነት ከሰጠን አመታት ተቆጠሩ፡፡ከወረዳ የምርጫ አስፈፃሚ ጀምሮ እስከላይ ያለው የምርጫ ቦርድ ሃላፊ፣ በገዥው መንግሰት ቀጥተኛ ተፅእኖ ስር መሆናቸው ግልፅ እና አሻሚ ያልሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከዘህ በላይ ማሣያዎችን ለማመላከት መሄድ ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ይሆናል ነገሩ፡፡

በመሆኑም ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአገራችን የለም፡፡ ሃቁ ይህ ሆኖ ሣለ ከተፈካካሪ የተቃወሚ ፓርቲዎች ጋር ኢሕአዴግ ለመርጫ እራሱን እያዘጋጀ ነው ማለት እንዴት ይቻላል ?
የገዥው መንገስት ቀጥተኛ ጫና በነፃ በጋዜጠኛ ላይ ፡-
ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ የመግለፅ ነፃነት አለው፡፡የሚለው በህገመንግስቱ አንቀፅ 29 ተፅፎ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል በህገ መንግስቱ ላይ ተገልፆ የተቀመጠ ሲሆን ገደብ ግን መሠረታዊ የሆነውን መረጃን የመስጠት እና የማግኘት እንዲሁም አስተሳሰብ ላይ ወይም አመለካከት ላይ ውጤት እንደማይኖረው በህገመንግስቱ ተገልፆ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ አሳብን በነፃ ማሰብና ማንሸራሸር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ አሳብን ለመግለፅ ይቅርና ከገዥው መንግስት ፍላጎት እና አሳብ ውጪ ማሰብ በራሱ ለእስራት እና ለእንግልት ይዳርጋል፡፡ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣በማሰር እና እንዲሰደዱ በማደረግ ኢትዮጵያ በዓለማችን መጥፎ ሪከረድ አስመዝግባለች፡፡በአሁን ወቅት ከ17 የማያንሱ ጋዜጠኞች በእስር ቤት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡21 የሚሆኑ ጋዜጠኖች በስደት መከራን እየተቀበሉ ነው፡፡መንግስትን ተችቶ የፃፈና ፁሁፉ የወጣበት ጋዜጣ ወይም መፅሔት ጨምሮ ሁሉም ተጠራርጎ ቃሊቲ የሚገባበት ወይም አደገኛ ዛቻና መስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡በውጪ አገር የሚገኙ የተለያዩ ሚዲያዎችም ቢሆኑ፣በአገር ውስጥ ተደማጭ እና ተነባቢ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ አፈና እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡

ስለዚህም ነፃ አሳብ የሚንሸራሸርባቸው ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ምን ያህል አሉ ? በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ተፈካካሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ የሚያደርጉት በይትኛው ነፃ ጋዜጣ እና መፅሔት ነው ? ህሊናውን እና ሙያውን ብቻ መሠረት አድርጎ የሚሰራ ጋዜጠኛ ምን ያህል አለ ? እርግጥ ይህ ፁሑፍ የቀረበበት ሚዲያ ጋዜጣ በቀጣይ የሌሎች ጋዜጣ እና ጋዜጠኞች እጣ ፈንታ እንደማይደረሰው በምንም እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡በምንም!!
እናም ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ጋዜጠኛ እና የእትመት ውጤት ሣይኖር መርጫ እንዴት ይታሰባል፡፡አገራችን በጋዜጠኛ ድርቅ እንድትመታ ገዥው መንግሰት ሆነ ብሎ ያደረገው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ይህ በሆነበት ሁኔታ ኢሕአዴግ ለመርጫ እራሱን እያዘጋጀ ነው ማለት በራስ ላይ እንደመተኮስ ይቆጠራል ፡፡

ከላይ በመጠኑ የዚህ ፁሑፍ አቅራቢ ለመዳሰስ የሞከራቸው እና ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኢሕአዴግ በጭራሽ እራሱን ነፃ ለሆነ የምርጫ ውድድር እያዘጋጀ አይደለም !የፖለቲካ ሊቃውንት እንደሚያስገነዝቡት እና ዓለም አቀፍ ነባሪዊ ሁኔታ የሚያመላክተው ለምርጫ መሰረታዊ ከሆኑት ውስጥ ፤በእኩል ደረጃ ባይወንም እንኳን በአንፃራዊነት የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ነፃነት እና እኩል ተሣትፎ ሊኖር ይገባል፣ፓርቲዎችን ሊያወዳደሩ የሚችል ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ ምርጫ ቦርድ እና ጉዳዩን ሙያዊ ስነምግባር መሠረት በማድረግ ለህዝብ መረጃ የሚያደርስ ነፃ ሚዲያ ያስፈልጋል፡፡እነዚህ መሰል ዋንኛ መስፈርቶች ባልተሟሉበት በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በመጪው ግንቦት ወር ነፃ ምርጫ ማካሄድ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !


No comments:

Post a Comment