Thursday, November 20, 2014

የጅማ ህዝብ ባገዛዙ መማረሩን ገለጸ

 ኢሳት ዜና :-የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፣ የገንዝብ ሚኒስትሩ ሶፍያን አህመድና የኦሮምያ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊው ከጅማ ዞን የተውጣጡ የተለያዩ ድርጅት ተወካዮችን በጊዜ አዳራሽ ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ህዝቡ በአስተዳደሩ ተስፋ መቁረጡንና ለውጥ የሚፈልግ መሆኑን ተናግሯል።
የምርጫ ቅስቀሳ በሚመስለው መድረክ ፣ አቶ ሙክታር ተሰብሳቢው የሚሰማውን እንዲናገር ፈቅደዋል። ነዋሪዎቹ በዞኑ ልማት የሚባል ነገር እንደሌለ፣ ከጅማ አጋሮ የተሰራው የአስፋል መንገድ ፈራርሶ ህዝቡ ከመቸገሩም በላይ በተለይም ወላዶች ወደ ጅማ ሆስፒታል በሚሄዱበት ጊዜ መንገድ ላይ እንደሚሞቱ ተግልጿል።
በከተማው የሚገኙ ወታደሮች ነዋሪውን እየገደሉና እያሰቃዩ መሆኑን በቅርቡ የተፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎችን በማንሳት አቤቱታዎችን አሰምተዋል።
በዞኑ የተስፋፋው ሙስና ከአቅማችን በላይ ሆኗል ያሉት ነዋሪዎች ባለስልጣኖች የሚሾሙት ግንዘብ ዘርፈው ፎቅ ለመስራት ወይም ድርጅት ለመክፈት ነው በማለት የመንግስት ባለስልጣናት በከተማው ውስጥ የሚቀሙዋቸውን ቤቶችና ቦታዎችን በዝርዝር በመግለጽ አቅርበዋል።
የህዝቡ ቁጣ ያስደነገጣቸው አቶ ሙክታር ከድር ከስብሰባው በሁዋላ የተለያዩ ባለስልጣኖችን ሴንትራል ሆቴል በመሰብሰብ፣ የህዝቡ ብሶት ከልክ ማለፉን እንደገለጹና አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶ የማረጋጋት ስራ እንዲሰራ አዘዋል።
በቅርቡ በአካባቢው የሰፈሩ ወታደሮች አንድ ወጣት እስከ አያቱ በሌሊት በጥይት ደብድበው መግለደላቸው መዘገቡ ይታወሳል። አርቲስ ወንዴ የተባለ ድምጻዊም እንዲሁ በወታደሮች ተደብድቦ ሆስፒታል ተኝቶ ሲታከም ከቆየ በሁዋላ፣ በአሁኑ ጊዜ በውጭ ሆኖ በማገገም ላይ ይገኛል።
ኢሳት አርቲስቱን ያነጋገረው ቢሆንም፣ አርቲስቱ እርሱና ልጁ በከፍተኛ ሁኔታ መደብደባቸውን በመግለጽ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ያመራ በመሆኑ፣ ከፍርድ ውሳኔ በፊት ለመናገር እንደሚከብደው ገልጿል።
በተመሳሳይ መልኩም በሃረር የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ በሚል አጀንዳ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ህዝቡ ተቃውሞውን አሰምቷል። መድረኩን የመሩት የክልሉ ፕሬዚዳንት እና ምክትላቸው ሲሆኑ ፣ ፕሬዚዳንቱ በያዝነው አመት ያጋጠሙ የመልካም አስተዳድር ችግሮችን ህዝቡ እንዲናገር በፈቀዱት መሰረት ተሰብሳቢው እድሉን
በመጠቀም ብሶቱን አሰምቷል። አንዳንድ ነዋሪዎች ” ልጆቻችን ስራ አጥ ሆነዋል፣ እዚህ አካባቢ ከ60 አመታት በላይ ብንኖርም አሁን ግን ስራ እንዳናገኝ ታግደናል፣ የት ሂዱ ነው የምትሉን?” በማለት በአካባቢው የሚታየው ዘረኝነት እንዳስመረራቸው ገልጸዋል።
ባድሜ ዘምተው በመቁሰላቸው በቦርድ የተሰናበቱ ወታደሮች ደግሞ መስተዳድሩ እውቅና እንደነፈጋቸውና መብቶቻቸው እንዳልተከበሩላቸው ተናግረዋል።
በከተማዋ ውስጥ ፍትሃዊ የልማት ስርጭት አለመኖሩን የገለጹት ነዋሪዎች፣ በተለይ መጤዎች በሚባሉት አካባቢዎች ምንም አይነት የመሰረተልማት አገልግሎት እንዳልተዘረጋላቸው በምሬት ገልጸዋል።
ህዝቡ በርካታ ጥያቄዎችን ቢያነሳም ፕሬዚዳንቱ ጥያቄዎችን በወረዳ ደረጃ ታገናላችሁ በማለታቸው ህዝቡ አዳራሹን እየለቀቀ ወጥቷል።


No comments:

Post a Comment