Friday, August 15, 2014

ኢ.ሕ.አ.ግ ያሰለጠናቸውን ሰራዊቱን አስመረቀ

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር አንግቦ የተነሳውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማዳን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ለዓላማቸው ጽኑ የሆኑና በወታደራዊ የጦር ስልት ከጠላት ጦር የላቀ ሠራዊት በማፍራት በሰሜን ምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል በተለያዩ ቦታዎች በወያኔ ላይ በሚያካሂዳቸው ውጊያዎች በጠላት ጦር ላይ ከባድ ውድመትን እያስከተለ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዳሜ ነሐሴ 3 ቀን 2006 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ለወራት በሽምቅ ውጊያ የወታደራዊ ሳይንስና በፖለቲካ መስክ ያሰለጠናቸውን የአርበኛ ሠራዊት ማስመረቁትን በስፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን የድርጅቱን ማሰልጠኛ ሃላፊ ጠቅሶ ዘግቧል።

የማሰልጠኛ ሃላፊው ለዘጋቢያችን እንደገለጹለት ከሆነ በአሁኑ ዙር የተመረቁት የአርበኛ ሰራዊት በተለያዩ የአየር ንብረቶች እና መልክዓ ምድሮች በቀንም ሆነ በለሊት በሚደረጉ ውጊያዎች በቀላሉ በጠላት ጦር ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት የሚያስችል የሽምቅ ውጊያ ወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሥራ-አስፈፃሚዎች በተገኙበት የተካሄደው በዚህ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ተመራቂ አርበኞቹ በስልጠና ወቅት በቀሰሙት ትምህርት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማዳን ተልዕኮን ከግብ ለማድረስ የበኩላቸውን አሰተዋጽኦ ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን እና ለዚህም ዓላማ መሳካት የህይወት መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አርበኛ መዓዛው ጌጡ ለተመራቂ አርበኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያሰተላለፉ ሲሆን ሊቀ-መንበሩ አክለውም “በዛሬው ዕለት የተመረቃችሁ አርበኞች በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ በአምባገነኑ ወያኔ አማካኝነት የተጋረጠውን የሕልውና አደጋ የመታደግ ትልቅ ኃላፊነት እና አደራ ያለባችሁ በመሆኑ ለቆማችሁለት ዓላማ በጽናት፣ በትዕግስትና በቆራጥነት የበኩላችሁን ድርሻ መወጣት አለባችሁ!” በማለት ለተመረቂ የአርበኛ ሰራዊት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


No comments:

Post a Comment