Sunday, August 10, 2014

የኢህአዴግ ዲሞክራሲና የቴሌ ኔትዎርክ ተመሳሰሉብኝ

እኔ የምለው … አንዳንድ የመንግስት ተቋማት በእነሱ ብሶ ለምንድነው ቁጣ ቁጣ የሚላቸው? (“የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” አሉ!) ከምሬ እኮ ነው… እኛ የተበደልነው አርፈን ተቀምጠን እነሱ እየተመላለሱ ይቆጡናል፡፡ (ኧረ “ፌር” አይደለም!) ያውም እኮ ሳንደርስባቸው ነው፤ ቤታችን ድረስ እየመጡ – በኢቴቪ መስኮት፡፡ ከሁሉም አንጀት የሚያበግነው ደግሞ ትላንት እኛው በድምፃችን ይመሩናል ብለን የመረጥናቸው ተወካዮቻችን፣ ማታ ማታ በቲቪ እየመጡ መቆጣታቸው ነው፡፡ (ለ90 ሚ. ህዝብ ማስጠንቀቂያ አይፃፍማ!) ይሄን ሁሉ ያስቀባጠረኝ የሰሞኑ የኢትዮ- ቴሌኮም ቁጣ የተቀላቀለበት መግለጫ ነው፡፡ (እኛ ሳንቆጣ እሱ ይቆጣን?!)
በእርግጥ መጀመሪያ የምስራቹን ነበር ያስቀደመው፡፡ ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹን በስኬት ማጠናቀቁን በድል አድራጊነት ስሜት አበሰረን፡፡ (የቴሌ ድል የእኛም ድል ነው!) እንደመሰለኝ… የቁጣው መንስኤ የኢቴቪ ጋዜጠኛ ጥያቄ ነው፡፡ “ደንበኞች አሁንም የአገልግሎት ጥራት ችግሮች አሉ እያሉ ነው” የሚል ጥያቄ ሳያነሳ አልቀረም – ጋዜጠኛው፡፡ (ግን እኮ አልዋሸም!) ይሄኔ ነው ቁጣ ቁጣ ያለው – “አገልጋያችን” ኢትዮ-ቴሌኮም፡፡
አያችሁ… እዚህ አገር ሁሉ ነገር የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ቢሆን እኮ የሚቆጣው ደንበኛ እንጂ አገልግሎት ሰጪው አይደለም፡፡ የሚቆጣው ህዝብ እንጂ መንግስት አይደለም፡፡ (መንግስትማ አገልጋይ ነው!) እኔ የምላችሁ… “ደንበኛ ንጉስ ነው” የሚለው አባባል እኛ አገር “ደንበኛ እርኩስ ነው” በሚል ተቀይሯል እንዴ? …በእርግጥ የኛ አገር ነጋዴዎች ወይም አገልግሎት ሰጪዎች “The Customer is always right” (ደንበኛ ሁሌም ትክክል ነው)  የምትለዋን አባባል ሲሰሙ “መስሎሃል!” እንደሚሉ ነገረ ስራቸው ያስታውቃል፡፡ እናም …ቢቆጡን፣ ቢያንገላቱን፣ መብራት ቢከለክሉን፣ ኔትዎርክ ቢነጥቁን፣ ውሃ ቢወስዱብን፣ ታክሲ የለም ቢሉን፣ ዘይት ቢያጠፉብን፣ ስኳር ቢያስወድዱብን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢፈጥሩብን ወዘተ… ዝም ብለን መቀበል ብቻ ነው፡፡ ለምን “ደንበኛ ንጉስ”  ሳይሆን “እርኩስ ነው”
እናላችሁ… የኢትዮ ቴሌኮሙ ኃላፊ በኢቴቪ መስኮት ገጭ ብለው የመንግስት “የገቢ ኩራት” ስለሆነው መ/ቤታቸው ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩ፡፡ የኔትዎርክ ማሻሻያው “ነዳጅ እንደሚበላ አሮጌ መኪና ሆነ” (አባባሉ የእኔ ነው!) ሲባሉ… አልካዱም፡፡ “በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ኔትዎርክ ይጠፋል” የሚለውን ቅሬታም ተቀብለዋል፡፡ በመጨረሻ ግን “እናስ ምን ይጠበስ?!” ዓይነት ምላሽ ነው የሰጡት፡፡ “ይሄን ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሰራ እኮ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ያጋጥማሉ” አሉን፡፡ (ኔትዎርክ በዓመት አንዴ ጠፋ ብለን የምንሞላቀቅ “ቅንጡዎች”  አደረጉን እኮ!) በመካያውም… “የኔትዎርክም ሆነ ሌሎች ችግሮች በሂደት ይፈታሉ” … ብለው ገላገሉን፡፡ ይሄኔ ነው ኢህአዴግ ነፍሴ ትዝ ያለኝ፡፡ ኢህአዴግ ሁሌም ዲሞክራሲው ተንገራገጨ ወይም መልካም አስተዳደሩ ተሰናከለ አሊያም የሰብዓዊ መብት አያያዙ እያሳጣን ነው…በተባለ ቁጥር “በሂደት ይፈታል” ይለናል፡፡ የእሱ አይደለም የገረመኝ፡፡ የቴሌኮም መድገም ነው፡፡ (አወያይ መመሳሰል አሉ!)
ለዚህም ነው የኢህአዴግ ዲሞክራሲና የቴሌ ኔትዎርክ የተመሳሰለብኝ፡፡ (ሁለቱም የኋሊት ነው የሚጓዙት ልበል!) ለማንኛውም በሂደት ይፈታል ተብላችኋል – ኔትዎርኩ!!

addis admas


No comments:

Post a Comment