Monday, March 16, 2015

ኢህአዴግ በመንግሥት በጀት ለካድሬዎችና አባላቱ ሥልጠና እየሰጠ ነው።

መጋቢት ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ ካድሬዎችን የሚያሰለጥነው አካዳሚ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ በመለስ ዜናዊ ስም የተሰየመው የአመራር አካዳሚ በመንግስት በጀት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአምስት ዙሮች 2ሺ 500 ያህል ከፍተኛ አመራሮችን፣ ከ30ሺ በላይ መካከለኛ አመራሮችን አሰልጥኗል፡፡

አካዳሚው ያለአንዳች ፈቃድ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም ሲሰራ ከቆየ በሃላ በ2006 ዓ.ም በሚኒስትሮች ደንብ ቁጥር 321/2006 ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠ/ሚኒስትሩ በማድረግ መንግሥታዊ ተቋም ሆኖ ተቋቁሟል፡፡



አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በሱሉልታ አካባቢ በ50ሺ ካሬሜትር ቦታ ላይ ዋና የማስልጠኛ ተቋሙን እየገነባ ሲሆን እስካሁን ከየመንግስት መ/ቤት የሚመረጡ ካድሬዎችን ለማሰልጠን በመምህርነት ሲያገለግሉ የነበሩት የመንግሥትና የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለለስልጣናት እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

አካዳሚው በሥራ አመራር ዕውቀት በቂ ሥልጠናና ልምድ ያላቸው አሰልጣኞች የሌሉት ሲሆን፣ ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በአመዛኙ አመራር ብለው የሚሰጡት ስልጠና በኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ላይ ብቻ ያተኮረና ሳይንሳዊ የአመራር ክህሎት ሥልጠናን ያላቀፈ ነው ብለዋል፡፡

ሥልጠና የወሰዱት አመራሮች ወደሲቪል ሰርቪስ መ/ቤቶች ሲመለሱ ሠራተኛውን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት፣ በለውጥ ሠራዊት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲሰሩ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም መንግሥታዊ ተቋማትና እንጀራ ፈላጊው ሰፊው ሠራተኛ የአንድ ፓርቲ መገልገያ እንዲሆኑ እየተገደዱ መሆኑን ያሳያል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።

በተጨማሪም ኢህአዴግ በመንግስታዊ አደረጃጀትና በመንግስትና በህዝብ በጀት የራሱን አባላትና ካድሬዎች በዚህ መልኩ ማሰልጠኑ ሕገወጥነት መሆኑን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ በመንግስት ወጪ በመላ አገሪቱ ለተሰማሩ የሚሊሺያ አባላት ስልጠና እየሰጠ ነው።

ሚሊሺያዎቹ በደህንነት መስሪያ ቤት በተቀረፀው የገጠር ሚሊሻዎች የምርጫ አፈፃፀም መመሪያ እየሰለጠኑ ሲሆን፣ መራጮች ኢህአዴግን እንዲመርጡ ለማስገደድ ሚሊሺዎች የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጡዋቸዋል።

ሚሊሺዎች በአንድ ለአምስት በተቀመጠው አደረጃጃት መሰረት መራጮችን ወደ ምርጫ ጣቢያ በመውሰድ ለኢህአዴግ ድምጽ መስጠታቸውን ያረጋግጣሉ። በኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ላይ ከማስፈራራት ጀምሮ ድብደባ እስከመፈጸም፣ ይህም ሆኖ ካልተገኘ ስውር በሆነ መንገድ ስለሚወስዱት ጥብቅ እርምጃ ስልጠና ይወስዳሉ። በአንዳንድ ክልሎች ሚሊሺዎች ቀደም ብሎ ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን፣ በሌሎች ክልሎች ደግሞ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ስልጠናው ተጠናክሮ እየተሰጠ ነው።


No comments:

Post a Comment